በህክምና ስህተት ምክንያት በህሙማን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ

55
መስከረም 6/2012 በህክምና ስህተት ምክንያት በህሙማን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል የተለያየ ስራ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ በህክምና ስህተት ምክንያት በህሙማን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በጤና ተቋማት የህሙማንን ደህንነት ማስጠበቅ እንደሚገባም አመልክቷል። የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የህሙማን ደህንንነት ቀን ''የህሙማን ደህንነት ቀዳሚ የዓለም ጤና ጉዳይ'' ሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተለያየ ስነ-ስርዓት ተከብሯል። የእግር ጉዞ፣ የፓናል ውይይት፣ ጧፍ በማብራት እንዲሁም ለሕሙማን ደህንነት በተመለከተ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መድረክ ተዘጋጅቷል። በሚኒስቴሩ የሜዲካል ሰርቪስ ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ሰማን  በዚህ  ወቅት እንደገለጹት፤ በህክምና ስህተት ምክንያት በህሙማን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በስፋት መሰራት አለበት። በተለይም በጤና ተቋማት የህሙማንን ደህንነት ማስጠበቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የህሙማን ደህንነት ቀን የሚከበርበት ዓላማ በህሙማን ደህንነት ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል። ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የሕሙማንና የጤና ሙያ ማህበራት፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የልማት አጋሮች ተቀናጅተው የህሙማንን ደህንነት ለመጠበቅ እንደሚቻል ተናግረዋል። ለህሙማን ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር የተቋማትና የባለሙያ እንዲሁም የሌሎች አጋሮችን ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን አመልክተዋል። 'የኢትዮጵያ የሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት' የተባለ እንቅስቃሴ በመጀመሩ ንጽህናቸውና ደህንነታቸው የተጠበቁ የጤና ተቋማትን የማፍራት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል። በተጨማሪም ''ደህንነቱ የተጠበቀ ቀዶ ሕክምና ሕይወትን ያድናል'' በተባለ እንቅስቃሴ  የቀዶ ሕክምና ክፍሎችን ደህንነት ማሻሻል መቻሉንና የመደኃኒት ደህንነትን ለማስጠበቅ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነም አቶ ያዕቆብ አመላክተዋል። ከዓለም የጤና ድርጅት በስነ-ስርዓቱ የታደሙት ዶክተር ፋሚ አህምድ የህሙማን ደህንነት ላይ የሚከሰቱ ክፍተቶች ታካሚ ላይ አካላዊ፣ አዕምሯዊና እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳት እንደሚያስከትል ጠቁመዋል። በዚህም ምክንያት ጉዳቱ ታካሚውን ብቻ የሚጎዳ ሳይሆን ለቤተሰብ እንዲሁም ለማህበረሰብና ለአገርም   ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ለከፍተኛ ወጪ እንደሚዳርግ ዶክተር ፋሚ ተናግረዋል። ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ከ 10 ህሙማን አንዱ በሆስፒታል ውስጥ ደህንነታቸው በአግባቡ ባለመጠበቁ ምክንያት ህክምና እየተከታተሉ እያለ ጉዳት እንደሚደርስባቸው መረጃዎች ያመላክታሉ። በዓለም ላይ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ህክምና ሚሊዮኖችን ለከፋ ጉዳት ከመዳረጉም በላይ በዓመት ከ42 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በህክምና ስህተት ምክንያት እንዲባክን ያደርጋል። የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው በዓመት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህሙማን ደህንነቱ ባልተጠበቀ የቀዶ ህክምና ስህተት ምክንያት ለህልፈተ ህይወት ይዳረጋሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም