የዓለም ምርጥ መምህር ልምዱን በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ሊያካፍል ነው

77

ኢዜአ፤ መስከረም 6/2012 ኬንያዊው የዓለም ምርጥ መምህር ልምዱን በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ሊያካፍል ነው።

በ2019 የዓለም ምርጥ መምህርነትን ያሸነፈው ኬንያዊው ፒተር ታቢቺ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ዋይት ሀውስ ውስጥ ተገናኝቷል።

ታቢቺ ኒውዮርክ ውስጥ በሚካሄደው 74ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝቶ ንግግር እንደሚያደርግም ይጠበቃል።

በመምህርነቱ ሙያ አሁን ለደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ ያበቃውን መንገድ ያስረዳል ተብሏል።

መምህሩ ከናይሮቢ በሰሜናዊ ምዕራብ አቅጣጫ 188 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የናኩሩ መንደር የኬሪኮ ሚክስድ ዴይ ሁተለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳይንስ ያስተምራል።

ትጉሁ መምህር ከወር ደመወዙ 80 በመቶውን በኬንያ ለሚገኙ የደሃ ቤተሰብ ተማሪዎች እንደሚሰጥ የዋይት ሀወስ ቃል አቀባይ ስቴፋኔ ጊርሻም በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

የደሃ ልጆች መማሪያ የሆነው ትምህርት ቤት በአሁኑ ወቅት በታቢቺ ጥረት የሳይንስ ውድድር ከሚያደርግ ምርጥ ትምህርት ቤቶች ተጠቃሽ ሆኗል።

የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ስቴፋኔ ጊርሻም “ለተማሪዎችህ ባለህ ቁርጠኝነትና ጠንክሮ በመስራት ያሳየኸው ውጤት ሁላችንንም ለበለጠ ትጋት የሚያነሳሳ ነው” ማለታቸውን  ቢቢሲ እና ዴይሊ ኔሽን ዘግበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም