እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናትን የመመዝገብ ስራ እየተካሄደ ነው

59
መስከረም 6/2012 በትግራይ ክልል እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ከ168 ሺህ በላይ ህጻናትን የመደበኛ ትምህርት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናትን የትምህርት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በመካሄድ ላይ ላለው የምዝገባ ስራ ወላጆች  የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ተጠይቋል፡፡ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ባህታ ወልደሚካኤል ለኢዜአ እንደተናገሩት በክረምት ወቅት በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች  በተደረገ ዳሰሳ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ 168 ሺህ ህጻናት በጥናት ተለይተዋል፡፡ ከዚህ በፊት ለህጻናት ብቻ ተብሎ እስከ ህዳር ይደረግ የነበረው ምዝገባ ዘንድሮ መስከረም 25 እንደሚያበቃ አስታውቀዋል። በዚህም ወላጆች ሳይዘናጉ ልጆቻቸው በጊዜ እንዲያሰመዘግቡና ትምህርት እንዲያስጀምሩ ሃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ማዕከላዊ ዞን አስተዳደር የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ መምህር ግደይ በርሀ በበኩላቸው በዞኑ እደሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት የመመዝገብ ስራ በተጠናከረ ሁኔታ እንደቀጠለ ነው፡፡ በዞኑ እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ ህፃናት መካከል እስካሁን 70 በመቶ መመዝገባቸውን ጠቅሰው እቅዱን ለማሟላት መምህራን እና ወላጆች በትብብር የቤት ለቤት ምዝገባ እያካሄዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገቡ ማድረግ ምክር ቤቶችም ከፍተኛ ሚና አላቸው ያሉት ደግሞ የላዕላይ ማይጨው ወረዳ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ወርቄ ገብረስላሴ ናቸው። በተለይ በገጠር በቀሌዎች ወላጆች ስራ እንዲያግዟቸው ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት አይልኩም ነበር ያሉት ወይዘሮ ወርቄ አሁን ግን ህብረተሰቡ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ በኩል መሻሻል እየታየበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በትግራይ ክልል የዘንድሮ የመማር ማስተማር ሂደት መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚጀመር ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም