የኢትዮጵያና የኢንዶኔዥያ ፓርላማ ልምድ ለመለዋወጥ ሚያስችል ውይይት አደረጉ

63

መስከረም 6 / 2012 ዓም የኢንዶኔዥያ የፓርላማ አባላት ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር የትብብር ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ።

የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከኢንዶኔዥያ ፓርላማ ልዑካን ጋር ውይይት አድርገዋል።

የኢንዶኔዥያ የፓርላማ አባላት ልዑካ ቡድን መሪ ዶክተር ሱርሃማን ሂዳያት ሁለቱ አገሮች የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ቢኖራቸውም ግንኙነታቸው የሚፈለገውን ያህል ውጤት አለማምጣቱን ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ የህዝብ ለህዝብና የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነቱ ጠንካራ ባለመሆኑ ነው ብለዋል።

ይህን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር አገራቸው ከኢትዮጵያ ፓርላማ ልምድ መቅሰም የምትፈልግ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገችው ያለውን አስተዋጽኦ ያደነቁ ሲሆን አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት አንዳላትም ገልጸዋል።

የአገራቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በኡላማዎች ምክር ቤት አማካኝነት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንም ዶክተር ሱርሃማን አስታውሰዋል።

በተለይ የፓርላማ ለፓርለማ ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ ኤምባሲ በኩል ውይይቶች የሚዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው የልዑካን ቡድኑ ከፓርላማው ልምድ ለመቅሰምና የዲፕሎማሲ ግንኙነቱን ለማጠናከር ያለውን ፍላጎት አድንቀዋል።

ስለ ምክር ቤቱ አሰራርና አባላት ደንብ እንዲሁም በአገሪቷ እየተካሄደ ስላለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማብራሪያ ሰጥተዋቸዋል።

የኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ ግንኙነት እኤአ በ1955 በኢንዶኔዥያ በተካሄደው የኢዥያ-አፍሪካ ጉባዔ ይጀምራል።

በወቅቱ ቀዳማዊ ኃይለስላሴና ልዑካቸው በጉባዔው ላይ ተሳታፊ እንደነበሩም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታቸውን የጀመሩት ግን እኤአ በ1961 መሆኑ ይነገራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም