የወሊሶ ደም ባንክ 6ሺህ ዩኒት ደም አከፋፈለ

121
አምቦ መስከረም 6 ቀን 2012 ዓም በተጠናቀቀው በጀት አመት ከበጎ ፈቃደኞች የተሰበሰበ 6ሺህ ዩኒት ደም ለጤና ተቋማት ተከፋፍሎ ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉን የወሊሶ ደም ባንክ አስታወቀ። የደም ባንኩ ኃላፊ ተወካይ አቶ ፍራኦል ረጋሳ ለኢዜአ እነደገለፁት ደሙ የተሰበሰበው በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ እንዲሁም በሰሜን ሸዋና በአዲስ አበባ ልዩ ዞኖች ከሚገኙ በጎ ፍቃደኞች ነው ። በዞኑቹ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እንዲሁም የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት ሠራተኞች በልገሳው መሳተፋቸውን ተናግረዋል ። "የተሰበሰበው ደም በአራቱም ዞኖች ለሚገኙ 17 ሆስፒታሎች  ተከፋፍሎ ጥቀም ላይ እንዲውል ተደርጓል " ብለዋል ። "ወላድ እናቶች፣ ህጻናትና በትራፊክ አዳጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የደም ተጠቃሚ ሆነዋል" ብለዋል ። እንደ አቶ ፍራኦል ገለጻ በበጀት አመቱ የተሰበሰበው ደም ከቀዳሚው አመት በ2ሺህ ዩኒት ብለጫ አለው። በአምቦ  አጠቃላይ ሆስፒታል አዋላጅ ነርስ ሲስተር ትግስት ፉታሳ" ከባንኩ  የተገኘው ደም የወላድ እናቶችን ህይወት ለመታደግ አስችሎናል" ብለዋል ። በሆስፒታሉ ሁለተኛ ልጃቸውን የተገላገሉት ወይዘሮ ፌኔት ንጉሴ በበኩላቸው " በወሊድ ወቅት የደም እጥረት አጋጥሟቸው  እንደነበር አስታውሰዋል ። "ከሆስፒታሉ በቀረበልኝ ደም የኔም የልጄም ህይወት ተርፏል" ብለዋል ። "የወላዶችን ህይወት ለመታደግ በየሶስት ወሩ ደም እየለገሰኩ ነው"ያሉት ደግሞ  የምዕራብ ሸዋ ዞን የሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ ናኦል ኢሬንሶ ናቸው። የወሊሶ ደም ባንክ በ2012 አመት 8 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ  አቅዶ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ1ሺህ 600 በላይ ዩኒት ደም መሰብሰቡ ታውቋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም