የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአክሲዮን አደረጃጀት ሊያቋቁም ነው-ፌዴሬሽኑ

55
መስከረም 5/2012  በዘንድሮው ዓመት ክለቦች በራሳቸው የሚተዳደሩበት አዲስ አወቃቀር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአክሲዮን ማህበር ሊቋቋም ነው ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ በሰጠው መግለጫ በዘንድሮው ዓመት ክለቦች በራሳቸው የሚተዳደሩበትን አዲስ የውድድር ስልት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ለማቋቋም የጥናት ሰነዱን ይፋ አደረገ። ፌዴሬሽኑ እንደገለጸው የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፕሮፌሽናል ለማድረግ አዲስ አደረጃጀት ያለውና 24 ክለቦችን በአባልነት የያዘ እንዲሁም በሁለት ምድብ የሚያሳትፍ የውድድር ስልት ተግባራዊ ለማድርግ ያለመ መሆኑን ገልጿል። በዚህም ባለፈው ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ሲገናኙ በስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ተስተውሎባቸዋል የተባሉ ቡድኖች ለአብነትም ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና እንዲሁም የአማራ ክልል ከትግራይ ክልል ክለቦች ጋር እንዳይገናኙ ይደረጋልም ተብሏል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ወይም 'ሊግ ካምፓኒ' የሚመሰረተው ፌዴሬሽኑን ጨምሮ 24 የክለብ አባላቶችን በመያዝ እንደሆነም እንዲሁ። የምስርታ ጉባኤው በመጪው መስከረም 13 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚከናወንም ይጠበቃል። የፌዴሽኑ የጥናት ሰነድ እንዳመለከተው አክሲዮኑ ሰባት የቦርድ አባላት ያሉት ሲሆን ክለቦቹ በሚያካሂዱት የምስረታ ጉባኤ ላይ አባላቱ በሚያስቀምጡት የአክሲዮን ሽያጭ መጠን እንደሚወሰንም ተገልጿል። የአክሲዮኑ አባላትም ባለፈው ዓመት ወደታችኛው ሊግ የወረዱትን ጨምሮ ዘንድሮ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የገቡትንና በሊጉ ሲሳተፉ የነበሩ ክለቦችን ያካተተ ነው። በተጨማሪም ከሁለቱ የከፍተኛ ሊግ ተሳታፊዎች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ አምስት ክለቦችንም ያካትታል ተብሏል። በአዲሱ የውድድር ስልት ከሁለቱ ምድብ አንደኛ የወጡት ክለቦች እርስ በእርሳቸው በገለልተኛ ሜዳ ሁለት ጨዋታዋችን በማድረግ ውድድሩ ይጠናቀቃል። አሸናፊው ክለብ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚካፈል ሲሆን በሁለተኛነት ያጠናቀቀው ክለብ ደግሞ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ እንደሚሳተፍ ፌዴሬሽኑ ያቀረበው የጥናት ሰነድ ይገልጻል። ቀደም ሲል በነበረው የውድድር ህግ በፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉት ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ የነበረ ክለብ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተካፋይ እንደነበር ይታወሳል። በአዲሱ የውድድር ስልት ግን የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ የሆነው ክለብ በተጋባዥነት የሴካፋ ዋንጫ ተካፋይ እንደሚሆንም ያመለክታል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ኮለኔል አወል አብዲራሂም በዚሁ ወቅት እንደገለጹት አክሲዮኑን ለማቋቋም የተለያዩ አገራት ተሞክሮ መወሰዱን በመጠቆም እግር ኳሱን ለማሳደግና የገቢ ምንጭን ለማስፋት ያለመ እንደሆነም ተናግረዋል። በዚሁ የአክሲዮን አደረጃጃት ክለቦቹን ትርፋማ ለማድረግ ሰባት ዘርፎችን በማቋቋም በዋና ዳይሬክተርነትና በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት እንዲመራ ይደረጋልም ብለዋል። ከነዚህም መካከል የውድድሮች ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት፣ የፋይናንስና የአስተዳደር፣ ምግብና አግሮ ኢንዱስትሪ ፣ የማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽን፣ የሆቴል ኢንቨስትመንትና የስፖርት ትጥቅና ቁሳቁስ ዘርፎች እንደሚዋቀሩ ተናግረዋል። እነዚህ ዘርፎችም የሚመሩት ፕሮፌሽናል በሆኑ ሰዎች መሆኑን ምክትሉ አክለው ገልጸዋል። አዲሱ የውድድር ስልት ወይም አክሲዮን የሴቶችን ፕሪሚየር ሊግና የወጣቶቹን ፕሪሚየር ሊግ እንደሚጨምርም በዚሁ ወቅት ተገልጿል። በክለቦች ቁጥር ማነስ የሚፈጠረውን የውድድር መቀነስ ለማካካስም ሌሎች የጥሎ ማለፍ ውድድሮችን ለማዘጋጀት እቅድ መያዙ ተገልጿል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም