በአደአደር ወረዳ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ተገልብጦ የሰው ህይወት አለፈ

66
መስከረም 5/2012 በአፋር ክልል አደአደር ወረዳ ዛሬ መለሰተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ ተገልብጦ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና 16 ሰዎች መጎዳታቸውን ፖሊስ አስታወቀ። የክልል ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ አደጋ መንሰኤ ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ ምክትል ኮማንደር መሃመድኑር አደም እንዳሉት አደጋው የደረሰው የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3-20420 አ.አ የሆነ ዶልፊኝ 17ሰዎችን አሳፍሮ ከኮምቦልቻ ከተማ ወደ ሎግያ ከተማ በመጓዝ ላይ እንዳለ ነው። ተሽከርካሪው ዛሬ ቀን ሰባት ሰዓት አካባቢ በአደአር ወረዳ ካሳጊታ ቀበሌ እንደደረሰ ነው የመገልበጥ አደጋ የገጠመው። በአደጋው ህይወቱ ካለፈው ሌላ 12 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በዱብቲ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል። ምክትል ኮማንደር መሃመድኑር እንዳመለከቱት ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው አራት ሰዎች ደግሞ በአደአር ጤና ጣቢያ ህክምና አግኝተው ወደየቤተሰቦቻቸው ተልከዋል። የሟቹ አስክሬንም ለቤተሰቦች መላኩንና አሽከርካሪውም ተይዞ የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን አስረድተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም