የአማራ ክልላዊ መንግስት የቢሮና ኤጀንሲ ስራ ኃላፊዎችን ሾመ

98
መስከረም 5/2012 ኢዜአ የአማራ ክልላዊ መንግስት የተለያዩ ቢሮዎችና ኤጀንሲን ለሚመሩ ለሰባት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ሹመት መስጠቱን አስታወቀ። የክልሉ መንግስት የርዕሰ መስተዳደሩ ጽህፈት ቤት  የህዝብ ግንኙነት  ዳይሬክተር አቶ አቻምየለህ ካሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ሹመቱ ስራን ማዕከል ባደረገ አግባብ አደራጅቶ ከመስራት ፅኑ ፍላጎት የተደረገ ነው። ከጳጉሜ 01/2011 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ቢሮዎችን በኃላፊነት የሚመሩ ሹመቶችን የክልሉ መንግስት መስጠቱን አስታውቀዋል። ሹመት ከተሰጣቸው መካከልም የክልልን ጤና ጥበቃ ቢሮ ይመሩ የነበሩትን ዶክተር አበባው ገበየሁን በመተካት ዶክተር መልካሙ አብቴ መሆናቸው ተመልክቷል። እንዲሁም የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ግዛት አብዩ የገጠር መሬት አስተዳድርና አጠቃቀም ቢሮ ኃላፊ ሆነው መሾማቸውን ገልፀዋል። የጎንደር ከተማ ከንቲባ የነበሩት ዶክተር  ሙሉቀን አዳነ  ደግሞ የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ሲሰሩ የቆዩት  አቶ ብርሀኑ ጣዕም ያለው ደግሞ የክልሉ ንግድ ገበያ ልማት ቢሮ እና ዶክተር  ማማሩ አያሌው ሞገስ በክልሉ የውሃ፣መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ ኃላፊነት ተሹመዋል። ዶክተር መለስ መኮንን የግብርና ቢሮ ኃላፊ እና  ዶክተር  አያሌው ወንዴ ደግሞ አዲስ ለተቋቋመው የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሀ ነክ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው እንዲያገለግሉ የተሾሙ ናቸው። ተሿሚዎቹ ኃላፊነታቸውን በቅንነትና በታማኝነት ህዝባቸውን እንዲያገለግሉም የክልሉ ርዕሰ መስተድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአደራ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም