በጎ ፍቃደኞች ባደረጉላቸው ድጋፍ ችግራቸው መቃለሉን በባሌ ዞን ተጠቃሚዎች ገለጹ

73
ጎባ ኢዜአ መስከረም 5/2012 በክረምት በጎ ፍቃደኞች የተደረገላቸው ድጋፍ ችግሮቻቸውን ለማቃለል እንደረዳቸው በባሌ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ ተጠቃሚዎች ገለጹ። ወይዘሮ ፀሃይኔሽ ወልደሚካኤል በጊኒር ወረዳ የቀበሌ አንድ ነዋሪ ሲሆኑ አቅመ ደካማ በመሆናቸው ባረጀና በፈራረሰ የሳር ቤት ውስጥ ህይወታቸውን ለመግፋት ሲገዱ መቆየታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል። በዚህም ብርድና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው ለበሽታ ታገልጸው እንደነበር አስታውሰዋል። “ችግሬን ያዩ የአካባቢው ነዋሪዎች ቤቴን ከሳር ክዳን ወደ ቆረቆሮ በመቀየራቸው ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፤ለረዱኝም ሰዎች ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ይባርክልኝ” በማለትምስጋና አቅርበዋል። በዲንሾ ወረዳ ልጆቻቸውን የለአባት እንደሚያሳድጉ የተናገሩት ወይዘሮ መዓዛ መስፍን በበኩላቸው በጎ ፍቃደኞቹ ገንዘብ በማዋጣት ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ እንደገዙላቸው ተናግረዋል። በዚህም በመበረታታት ልጆቻውን አስተምረው ለማብቃት እንደሚጥሩ ገልጸዋል። የአካባቢያቸው በጎ ፈቃደኛ የእሳቸውን ጨምሮ ለሶስት ወጣቶች ለንግድ አገልግሎት የሚውል ሞተር ብስክሌት ገዝተው እንደሰጧቸውና በዚህም በመጠቀም የገቢ ማስገኛው ስራ ላይ መሰማራታቸውን የተናገረው ደግሞ የሰዌና ወረዳ ነዋሪ ወጣት ሀሰን ከድር ነው። ወጣቱ “ ቤተሰቦቼ አቅመ ደካሞች ስለነበሩ በሰው ሞተር ብስክሌት በቀን ሰራተኝነት ተቀጥሬ እሰራ ነበር ፤ አሁን ላይ በጎ ፈቃደኛው ወጣቶች 75ሺህ ብር በማዋጣት ስለገዙልኝ ከራሴም አልፌ ቤተሰቦቼን ለመርዳት እየሰራሁ ነው” ብሏል። በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተሰማርተው ከነበሩት መካከል በጊኒር ወረዳ የቀበሌ ሁለት ነዋሪ ወጣት እክራም አብዱልቃድር በበኩሏ “በአገልግሎቱ በመሰተፌ አቅመ ደካሞችን በመርዳት የዜግነት ኃላፊነቴን ለለመወጣት ጥረት አድርጌያለሀ፤ በዚህም የህሊና እረፍት ይሰማኛል” ብላለች። ለተቸገሩ ወገኖች የምትሰጠው ድጋፍ እንደምትቀጥልበትም ተናግራለች። “ሰዎች ባላቸው አቅም መልካም ነገርን ካበረከቱ ሀገራችንን መለወጥ እንችላለን” በሚል እምነት ላለፉት ሁለት ወራት በተለያዩ የስራ መስኮች ማገልገላቸውን የተናገረው ደግሞ የሰዌና ወረዳ ነዋሪ አህመድ በከር ነው። በቀጣይነትም የአካባቢያቸውን ወጣቶች በማስተባበር በዘመቻ መልኩ የጀመሩትን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በየወሩ በመደበኛነት እንደሚቀጥሉበት ገልጿል። ወጣቱ እንዳለው በተለይ አቅም የሌላቸው ሰዎች ቤት በመገኘት ገንዘብ በማዋጣት አገልግሎቱን ለማስቀጠል ፍላጎታቸው ነው። የሰዌና ወረዳ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሰአዳ ኡመር በበኩላቸው ህብርተሰቡን አስተባብረው የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ባስመዘገቡት የተሻለ አፈጻጸም በዞን ደረጃ የዋንጫ ተሸላሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። የዞኑ ሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፈይሴ አለሙ እንዳሉት በዞኑ በክረምት ወራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ጨምሮ ከ250 ሺህ የሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በበጉ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ተሳትፈዋል። በዚህም ከተከናወኑት መካከል ችግኝ ተከላ፣ደም ልገሳ፣የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት፣ የመንገድ ጥገናና የማጠናከሪያ ትምህርት ይገኙበታል። በአገልግሎቱ መንግስት ሊያወጣ የነበረውን ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችሏል፤ ከ989ሺህ  የሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎችም ተጠቃሚ መሆናቸውንም ወይዘሮ ፈይሴ አብራርተዋል። የባሌ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ በበኩላቸው የበጉ ፈቃድ አገልግሎት ከገዳ ስርዓት እሴቶች ውስጥ አንዱ መሆኑ ተናግረዋል። “በዘመቻ መልኩ በክረምት ወራት ብቻ የነበረውን ተግባር በሌላውም ወቅት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲሰራ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው “ብሏል። በአገልግሎቱ የሚሳተፉትን ለማበረታታት የሚሰጠው የእውቅና መርሃ ግብር እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም