የአፍሪካ ትናንሽ አጥቢ እንስሳት ሲምፖዚየም በመቀሌ እየተካሄደ ነው

61
መስከረም 5/2012 13ኛው የአፍሪካ ትናንሽ አጥቢ እንስሳት ሲምፖዚየም በመቀሌ ዩኒቨርሲቱ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው። በሲምፖዚየሙ ከ25 ሃገራት የተውጣጡ አለም አቀፍ ተማራማሪዎች እየተሳተፉ ሲሆን ለአምስት ቀናት እንደሚቆይና ከ100 በላይ ጥናቶች እንደሚቀርቡ ይጠበቃል። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በአለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ተቋማት እየታገዘ በርካታ ጥናቶች እያካሄደ ይገኛል። በዩኒቨርሲቲው አዘጋጅነት ዛሬ የተጀመረው ሲምፖዚየሙ ተቋሙ ለሚያካሂዳቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች እንደ ግብአት ለመጠቀም እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል። "የሲምፖዚየሙ ዓላማ በአራት ዓመት ውስጥ በትናንሽ አጥቢ እንስሳት  የተሰሩ አዳዲስ ጥናቶችን የምከለሱበት ነው" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የአነስተኛ አጥቢ እንስሳት ተማራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ዮናስ ናቸው። ኢትዮጵያ በአጥቢ እንስሳት ከአፍሪካ ቀዳሚ እንደሆናቸው ገልጸው በሃገሪቱ ብቻ የሚገኙ 43 የሚሆኑ ትናንንሽ አጥቢ እንስሳት ለሌላው አለም ለማስተዋወቅ  ሲምፖዚየሙ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል። በስምፖዚየሙ ከሚቀረቡ ጥናቶች መካከል "የትናንሽ አጥቢ እንስሳት ዝሪያና ስርጭት በኢትዮጵያ" የሚል ይገኝበታል ። ከአፍሪካ ፣አውሮፓ ፣ሰሜንና ደቡብ አሜሪካና እስያ አህጉሮች የተወጣጡ ከ100 በላይ ተመራማሪዎች በሲምፖዚየሙ እየተሳተፉ እንደሆነ ተመልክቷል። 12ኛው ስምፖዚየም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 በማንታሷ ማዳጋስካር/Mantasoa, Madagascar/ መካሄዱን ጠቅሶ ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም