የኤች አይ ቪ ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ መጠኑን ለመቀነስ ያለመና 'ፕሪጋርት' የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

519
አዲስ አበባ መስከረም 5/2012 የኤች አይ ቪ ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ መጠኑን ለመቀነስ ብሎም ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ያለመና 'ፕሪጋርት' የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ። ፕሮጀክቱ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነትና በአራት የትምህርት ተቋማት ቅንጅት የሚከናወን ሲሆን በኢትዮጵያና ኡጋንዳ ባሉ ጤና ተቋማት የሚተገበር ይሆናልም ተብሏል። ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ በሚገኙ 10 ሆስፒታሎች እንዲሁም በኡጋንዳ ባሉ ሶስት የጤና ተቋማት የሚተገበር መሆኑም ታውቋል። በኢትዮጵያ ለሚተገበረው ፕሮጀክት የአውሮፓ ህብረት 4 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተገልጿል። የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኢንጂነር ፍስሃ ጌታቸው በዚሁ ወቅት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን እየከወነ ነው። ኤች አይ ቪ ኤድስ ከእናቶች ወደ ህፃናት የመተላለፍ መጠኑን ለመቀነስና ለመቆጣጠር የሚረዱ የተሻሻሉ መድሃኒቶችን በመጠቀምም በኤች አይ ቪ በተጠቁ እርጉዝ እናቶች ላይ በተመረጡ ሆስፒታሎች ጥናት እንደሚካሄድም ተናግረዋል። ዛሬም የመርሃ ግብሩ መነሻ ውይይት መካሄዱን ገልፀው በሚደረገው ጥናት የሚገኘው ግኝትም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚጠቅም መሆኑንም አስረድተዋል። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የተሻሻለና ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል መድሃኒት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አብራርተዋል። በመርሃ ግብሩ ከሚሳተፉ ተቋማት ውስጥ አንዱ በሆነው በስዊድኑ ካሮኒስካ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር እሌኒ አክሊሉ በበኩላቸው ባለፉት 20 ዓመታት ከእናቶች ወደ ልጅ የሚተላለፈውን የኤች አይ ቪ ኤድስ መጠን ለመቀነስ የተለያዩ የምርምር ስራዎች እየተሰሩ ነበር ብለዋል። 90 በመቶ ህፃናት በኤች አይ ቪ የሚያዙት ከእናት ወደ ልጅ በሚተላለፈው ነው ያሉት ፕሮፌሰሯ፤ የሚተላለፈውም በእርግዝና ወቅት፣ በወሊድ ጊዜ እንዲሁም ጡት በማጥባት ጊዜ መሆኑንም አስረድተዋል። የፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ መድሃኒትን የሚወስዱ እናቶችና እርጉዝ ሴቶች ህፃናቱ የመያዝ እድላቸው ወደ 5 በመቶ ዝቅ እንዲል ያደርጋልም ብለዋል። የፕሮጀክቱ ዓላማም ደህንነታቸውና ውጤታማነታቸው የተረጋገጡና የተሻሻሉ መድሃኒቶችን በመጠቀም የህፃናትን የመያዝ እድል ወደ ዜሮ ለማውረድ ያለመ መሆኑን ገልፀዋል። የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ፕሮጀክቱ ኤች አይ ቪ ከእናቶች ወደ ህፃናት እንዳይተላለፍ መንግስት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ ነው ብሏል። በሚኒስቴሩ የሚኒስትር ዴኤታ ፅህፈት ቤት አማካሪ አቶ ግርማ አሸናፊ እንዳሉት መንግስት በኤች አይ ቪ ኤድስ ዙሪያ ባከናወናቸው ስራዎች ለውጥ እየመጣ መሆኑን ተናግረዋል። ከፖሊሲና ስትራቴጂ ጀምሮ ኀብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ ተግባራት በቫይረሱ ሳቢያ የሚከሰት ሞትን 50 በመቶ መቀነስ መቻሉንም ገልፀዋል። የዛሬው ፕሮጀክትም ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከልትልቅ ድርሻ ያለውን የፀረ ኤችአ ይ ቪ ኤድስ መድሃኒት በመጠቀም ህክምናውን ለእናቶች በመስጠት ወደ ፅንሱ እንዳይተላለፍ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የሚያስችል የጥናት ስልት ነው። ሚኒስቴሩ ለፕሮጀክቱ ድጋፍ ላደረጉና እውን እንዲሆን ለሚሰሩ አካላት ምስጋና እንደሚቸርና አብሮ ለመስራትም ዝግጁ መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም