የነዳጅ ፍለጋን በማጠናከርና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችትን በማወቅ ወደምርት ለመግባት የሚያስችል የነዳጅ ሥራዎች ፖሊሲና አዋጅ ተዘጋጀ

110
መስከረም 5/2012 በኢትዮጵያ የነዳጅ ፍለጋን ለማጠናከር፣ በአገሪቱ ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ለማወቅና ወደምርት ለመግባት የሚያስችል የነዳጅ ሥራዎች ፖሊሲና አዋጅ ተዘጋጀ። በማዕድንና ነዳጅ ሚኒሰቴር በተዘጋጁት የነዳጅ ፖሊሲና አዋጅ ረቂቆች ላይ የመከረ የባለድርሻ አካላት  ውይይት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል። የፖሊሲውና አዋጁ አስፈላጊነትን፣ የሚጠበቁ ውጤቶችንና ተግባራዊነታቸውን የተመለከቱ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል። በተለይ የፖሊሲው መውጣት በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የነዳጅ ፍለጋ ስራ ከማጠናከር ባለፈ የአገሪቱን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ለማወቅና ወደምርት ለማስገባት የላቀ ጠቀሜታ አለው ሲሉ በሚኒስቴሩ የነዳጅ ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክተር ዶክተር ቀጸላ ታደሰ በውይይቱ ላይ አስረድተዋል። በመስኩ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብም ያግዛል ብለዋል። የነዳጅ አልሚዎች ተሳትፎን ውጤታማ ማድረግ፣ በዘርፉ ልማት ዙሪያ በፌደራልና ክልል መንግስታት መካከል የተቀናጀ አሰራር መዘርጋት ከፖሊሲው ዓለማዎች መካከል ይጠቀሳሉ። ከዘርፉ ጋር በተያያዘ የአገር ውስጥና የቀጣናውን የገበያ ዕድል በመዳሰስ የተሻለ የገበያ አማራጭ መፈለግና ተወዳዳሪ የሆነ የገበያ ስርዓት መዘርጋትም እንዲሁ ሌሎቹ ዓላማዎች ናቸው። ዶክተር ቀፀላ እንደተናገሩት፤ ለነዳጅ ፍለጋ አመቺ ናቸው የተባሉ አካባቢዎች፣ ፍለጋው የሚካሄድበት መንገድ፣ በፍለጋው ህዝቡንና አካባቢውን በማይጎዳ መልኩ የአገርን ጥቅም እንዴት ማስጠበቅ ይቻላል የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችም በፖሊሲው ጥናት ተዳሰዋል። ፖሊሲው ኢትዮጵያዊያን በዘርፉ ስልጠና የሚወስዱበትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማረጋገጥ የሚቻልበት  አቅጣጫዎችን ያመላከተ ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የተረቀቀው የነዳጅ ሥራዎች አዋጅ ደግሞ በ1978 ዓ.ም የወጣውን አዋጅ የሚተካ እንደሆነ ነው ዶክተር ቀፀላ ያብራሩት። በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ለረጅም ጊዜ የቆየ ከመሆኑ ጋር የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያስተናግድ ባለመሆኑ እንዲሻሻል  ሆኗል ብለዋል። የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ኳንግ ቱትላም በበኩላቸው፤ አገሪቷ በዘርፉ ፖሊሲ አልነበረታም ሲሉ ጠቅሰው በዚህም የተነሳ በነዳጅ ፍለጋ ላይ የሚሰማሩ ኩባንያዎችን በሚጠበቀው መጠን መሳብ አለመቻሉን ተናግረዋል። ዶክተር ኳንግ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በነዳጅ ፍለጋ ተግባር ተሰማርተው የሚገኙት ኩባንያዎች ከአምስት አይበልጡም። በመሆኑም በመስኩ ፖሊሲና የነዳጅ ሥራዎች ረቂቅ መዘጋጀቱ እነዚህን የመሳሰሉ መሰረታዊ ችግሮችን እንደሚፈታ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶማሌ ክልል ነዳጅ መገኘቱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል። በሶማሌ ክልል በኦጋዴን 6 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ድፍድፍ ነዳጅ ክምችት አለ ተብሏል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም