የወርልድ ቴኳንዶ የዳን ደረጃ ማሻሻያ ፈተና ተጀምሯል

152
አዲስ አበባ መስከረም 5/2012 የወርልድ ቴኳንዶ የዳን ደረጃ ማሻሻያ ፈተና ዛሬ በብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ጽህፈት ቤት ቅጥር ውስጥ በሚገኘው የወርልድ ቴኳንዶ ጅምናዚየም መስጠት ተጀምሯል። ፈተናው ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት ይቆያል። ከሰባት ክልልና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 300 የሚደርሱ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርተኞችና አሰልጣኞች ፈተናውን እንደሚወስዱ ተገልጿል። ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ዳን የሚሰጠው የዳን ደረጃ ማሻሻያ ፈተና በስምንት አሰልጣኞች የሚሰጥ ይሆናል። ስፖርተኞቹና ሰልጣኞቹ የሚወስዱት የተግባር ፈተና ሲሆን በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ውስጥ ያሉ ጥበቦችና የፍልሚያ አይነቶች በማሳየት ነጥብ የሚያገኙ ይሆናል። የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ተቋም በዳን የደረጃ ማሻሻያ ፈተናው ላይ ለሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ጥሪ መቅረቡን ለኢዜአ ገልጸዋል። ነገር ግን የኦሮሚያና የአማራ ክልል አሰልጣኞች በየክልላቸው መጥተው ፈተናውን እንዲሰጡ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል። ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ባለፈው ዓመት ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት አሰልጣኞች ክልል ድረስ ሄደው እንዲፈትኑ 100 እና ከዚህ በላይ ተፈታኝ ሊኖራቸው እንደሚገባ መወሰኑን አስታውሰዋል። በዚሁ መሰረት ስልጠናው በኦሮሚያ ክልል መስከረም 10 እና 11 ቀን፣ በአማራ ክልል መስከረም 20 እና 21 ቀን 2011 ዓ.ም ለስፖርተኞናች ለአሰልጣኞች እንደሚሰጥ አመልክተዋል። ሌሎች ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች አዲስ አበባ በሚሰጠው ፈተና እየተሳተፉ እንደሚገኙም አቶ ፍቅሩ ገልጸዋል። የዳን የደረጃ ማሻሻያ ከተካሄደ በኋላ ፈተናውን ያለፉትና ደረጃቸውን ያሻሻሉ ስፖርተኞችና አሰልጣኞች ስም ዝርዝር በጥቅምት 2012 ዓ.ም ደቡብ ኮሪያ ለሚገኘው ዓለም አቀፉ የወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሸን እንደሚላክ አስረድተዋል። የዓለም አቀፉ የወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የተላከውን የፈተና ውጤት ካጣራ በኋላ ለስፖርተኞቹና አሰልጣኞቹ የዳን ደረጃ ማሻሻላቸውን የሚያሳይ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደሚልክም ጠቁመዋል። የዳን የደረጃ ማሻሻያ ፈተና በዓመት አንድ ጊዜ መስጠት ሁሉንም ተደራሽ የሚያደርግ በመሆኑ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በዓመት ሁለቴ መስጠት እንደጀመረና ዘንድሮውም ሁለተኛው ፈተና በጥር ወር 2012 ዓ.ም እንደሚሰጥ ተናግረዋል። የዳን ደረጃው ፈተና አዲስ አበባ ብቻ መሰጠቱ ሌሎች ክልሎች ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋቸው መሆኑና ፈታኞች ከአዲስ አበባ ብቻ መሆናቸው በስፖርተኞችና በአሰልጣኞች ቅሬታ ሲነሳበት የነበረ ጉዳይ እንደነበርም አመልክተዋል። ቅሬታዎቹን ለመፍታት ከ100 እና ከዚያ በላይ ተፈታኝ ላላቸው ክልሎቸ ባለሙያዎችን በመላክ እንዲፈተኑ እየተደረገ መሆኑንና ከሌሎች ክልሎች አስፈላጊውን መስፈርት ያሟሉ አሰልጣኞችም በፈታኝ ኮሚቴ እንዲካተቱ መደረጉን ጠቅሰዋል። እንደ አቶ ፍቅሩ ገለጻ የዳን ደረጃ ማሻሻያ ፈተናው ስፖርተኞች ራሳቸውን በእውቀትና በቴክኒክ ጊዜ ወደ ጊዜ እንዲሻሻሉ አንዲሁም ለአሰልጣኞች የሙያ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያግዝ ነው። አሰልጣኞች ባገኙት የብቃት ማረጋገጫ የማሰልጠኛ ማዕከላትን በመክፈት ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራትና የገቢ ምንጫቸውን ለማሳደግም ይረዳቸዋል ብለዋል። በኢትዮጵያ ከፍተኛው የዳን ደረጃ ስድስተኛ ዳን እንደሆነና ማስተር አዲሱ ኡርጌሳ ብቸኛው የዚህ ደረጃ ባለቤት እንደሆኑ ጠቅሰው ሌሎች አሰልጣኞችም ስድስተኛ ዳን ፈተና ለመያዝ ወስደው ውጤት እየተጠባበቁ መሆኑን አመልክተዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የወርልድ ቴኳንዶ የመጨረሻው የዳን ደረጃ ዘጠነኛ ዳን ነው። የኮሪያ የባህል ስፖርት በሚል የሚታወቀው ወርልድ ቴኳንዶ ከሰውነት ፍልሚያ ባሻገር ጥበባዊ ስልቶችን ያካተተ ክንዋኔ ሲሆን አእምሮና ሰውነት ማሰልጠንን ጨምሮ ህይወትን በአግባቡ ለመምራት የሚያግዝ የስፖርት ዓይነት እንደሆነ ይነገራል። የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በ1995 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን ስፖርቱ ከአትሌቲክስ በመቀጠል በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ ውጤት በማስገኘት አገሪቷን በማስጠራት ላይ ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም