የአልጣሽ ብሄራዊ ፖርክን በውጪ ሀገር ቱሪስቶች ለማስጎብኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው

68
መስከረም 5/2012 በምእራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ የሚገኘው የአልጣሽ ብሄራዊ ፓርክ በአዲሱ አመት ለመጀመሪያ ጊዜ በውጪ ሀገር ቱሪስቶች ለማስጎብኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ኤፍሬም ወንድም ለኢዜአ እንደተናገሩት ፓርኩ ከአምስት ዓመት በፊት በብሄራዊ ፓርክነት የተከለለ ቢሆንም በቱሪስቶች እየተጎበኘ አይደለም። ባለፉት ዓመታት በፓርኩ ቱሪስቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የመንገድ ግንባታ፣ የቱሪስት ማረፊያና የስካውት ቤቶችን የማደራጀት ስራ ሲከናወን መቆየቱን ገልፀዋል፡፡ በተለይ ከሁለት አመት በፊት በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ ለፓርኩ መዳረሻነት የተጀመረው የ16 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የጠጠር መንገድ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ተናግረዋል፡፡ ፓርኩን ለመጎብኘት ለሚመጡ ቱሪስቶች ጥበቃ የሚያደርጉ፤ መንገድ የሚመሩና የሚያጅቡ 91 እስካውቶች በፓርኩ የተለያዩ አካባቢዎች በቋሚነት መመደባቸውን ተናግረዋል፡፡ በተደረገው ዝግጅትም በ2011 ዓ.ም 11 የሚሆኑ የውጪ ሀገር ዜጎች ለጥናትና ምርምር ስራ በፓርኩ የወራት ቆይታ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ ጅምር እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ለማስቀጠልም በአዲሱ የበጀት ዓመት ፓርኩን በስፋት በማስተዋወቅ 200 በሚሆኑ የውጭ ሃገራት ቱሪስቶች ጉብኝት እንዲካሄድ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ሃላፊው አስታውቀዋል። ፓርኩ በርካታ ብዝሃ ህይዎት ያለው ቢሆንም ለከብቶቻቸው ግጦሽ ፍለጋ በሱዳን በኩል ወደ ፓርኩ የሚገቡ ፈላታ የተባሉ የናይጄሪያ አርብቶ አደሮች ጉዳት እያደረሱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ የቋራ ወረዳ ነዋሪ አቶ አይሸሹም ተስፉ በሰጡት አስተያየት ፓርኩ በብሄራዊ ደረጃ ሲከለል ለአካበቢው የተሻለ ገቢ ያስገኛል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ ከመከለሉ ውጭ በቱሪስቶች አለመጎብኘቱ ቅር እንዳሰኛቸው ገልፀው፤ በዚሁ ጉዳይ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ የአልጣሽ ብሄራዊ ፓርክ 2ሺ 566 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በውስጡም ቀጭኔና ዝሆንን ጨምሮ ከ30 በላይ አጥቢ የዱር እንስሳትና ከ180 በላይ የአዕዋፋት ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም