የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የ“ጊፋታ አዋርድ” ሽልማት ተበረከተላቸዉ

86
ሶዶ  መስከረም 5/2012 የቀድሞው  ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ “ ጊፋታ አዋርድ” የተሰኘ የምስጋናና የዕዉቅና ሽልማት ተበረከተላቸዉ፡፡ በወላይታ ሶዶ “አርአያዎቻችን በረከቶቻችን ናቸው” በሚል መርህ ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የምስጋናና ዕውቅና ስነ-ስርዓት ተካሂዷል፡፡ በስነ-ስርዓቱ ወቅት አቶ ኃይለማርያምን ጨምሮ በተለዩ አምስት ዘርፎች በሃገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጎ ተጽዕኖ የፈጠሩ 45 ግለሰቦች የምስጋናና የዕውቅና ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል፡፡ የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ አንዱአለም ሳይዳ እንደገለጹት መቻቻል፣ መከባበር፣ይቅርታ፣እርቅና መሰል የብሄሩ ዕሴቶችን በማጎልበት የተጀመረውን ሃገራዊ የለውጥ ጉዞ ለመደገፍ ዓላማ ያደረገ ስነ-ስርዓት ነው፡፡ አካባቢው በዕውቀትና በልምድ በሃገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ በጎ ተጽዕኖ የፈጠሩ ግለሰቦች የወጡበት ቢሆንም በተለያዩ ምክንያች እርስ በርስ የመነጋገር፣የመከባበርና ለጋራ ዓላማ በአንድነት የመነሳት ዕድሎች እንዳለነበሩ አስታውሰዋል፡፡ በአዲሱ ዓመት በይቅርታ ታድሶ ለህዝብ የሚሆኑ ተግባራትን ለመፈጸም ለሰሩ ዕውቅና በመስጠት በቀጣይ ተያይዘው ለመቀጠል ስነስርዓቱ መሰናዳቱን አስረድተዋል፡፡ ይህም የግለሰቦቹን ዕውቀት፣ ክህሎትና ልምድ ተከትሎ ለበጎ አስተዋጽኦ ራሳቸውን የሚያዘጋጁ ሌሎች ወጣቶችን በማፍራት በአካባቢው የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን በጋራ ለመመለስ ይረዳል ተብሏል። በፖለቲካ፣ በንግድና ቢዚነስ፣ በኪነ-ጥበብ ፣በትምህርት ፣ባህልና ኃይማኖትና ህክምናው ዘርፎች ከአካባቢ እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ በጎ አስተዋጽኦ የነበራቸው 45 ግለሰቦች ለመጀመሪያ ዙር እንዲታወሱና እንዲመሰገኑ ሽልማቱ እንደተሰጣቸው ተደርጓዋል፡፡ በኃይማኖቱ እነ አቡነ ተክለ-ኃይማኖትና አባባ ዋንዳሮን ጨምሮ በህይወት የሌሉ ነገር ግን አከባቢውን በበጎ መልኩ ያስተዋወቁ ሽልማቱና ዕውቅናዉ ከተበረከተላቸው መካከል ተጠቅሰዋል፡፡ በፖለቲካ አመራርና በትምህርት በሌሎች ጉዳዮች እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማበረከቱት አስተዋጽኦ ሽልማቱ የተበረከተላቸው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝና ባለቤታቸዉ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ናቸው፡፡ ለአቶ ኃይለማሪያ በአካባቢው ባህል መሰረት በፖለቲካው የአመራር ብስለትና ክህሎት በቀጣይም ከአብራኩ መሪ አይጥፋ በሚል የሚሰጥ ጦር፣ጋሻና የፈረስ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨረሲቲ እንዲመሰረት ላበረከቱት አስተዋጽኦ በእጅ ጥልፍ የተሰራ ምስል ተሸልመዋል። አቶ ኃይለማሪያም ሽልማቱን ከተቀበሉ በኋላ የተዘጋጀው ስነስርዓት በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥና የአንድነት ጉዞ ለማጠናከር የጎላ አስተዋጽኦ አንደሚኖረት ተናግረዋል። "ጊዜው የይቅርታ ነው"  ያሉት አቶ ኃይለማሪያም በነበራቸው የስልጣን ቆይታ ወቅት የተፈጠሩ ስህተቶችን ህዝቡ ይቅር እንዲላቸው በመጠየቅ በቀጣይም ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት መሪዎች በበኩላቸው ወጣቶች የሠላም፣የመቻቻል ፣ የመከባበርና ሰርቶ የመለወጥ ባህል እንዲያጠናክሩ መክረዋል። በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህዝባቸው ደህንነት፣ ሰላምና ብልጽግና በጋራ ለመስራት እጅ ለእጅ ተያይዘው በጋራ ለመስራት ቃል ገብተዋል፡፡ በስነስርዓቱ ወቅት የዞን ፣የክልል፤የሃገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ቦታዎች በከፍተኛ የስራ ኃላፊነትና ሙያ ላይ የተሰማሩ የወላይታ ብሄር ተወላጆች ተሳትፈዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም