የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስጌን ጥሩነህ ድንገተኛ ጉብኝት አካሄዱ

91
መስከረም 5/2012 በአማራ ክልል የመንግስት ሰራተኛው ስራውን በአግባቡ እንዳያከናውን የሚያደርጉ ችግሮችን የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ገለጹ። ርዕሰ መስተዳደሩ ዛሬ በክልሉ አራት አግልግሎት ሰጪ ተቋማት ድንገተኛ የስራ ጉብኝት አካሂደዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ተመስጌን ጥሩነህ የክልሉን ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ፣ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ፣ ሰላምና ደህንነት ቢሮ እና የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን  ጎብኝተዋል። ጉብኝታቸው ካጠናቀቁ በኋላ ርእሰ መስተዳድሩ እንደገለፁት የጉብኝቱ አላማ  በየተቋማቱ የሚስተዋለወን የአሰራር ክፍተት በመለየት አሰራሮች እንዲሻሻሉ ለማድረግና ጠንካራ ጎኖችን ደግሞ ለማበረታትት ነው። በጉብኝታቸው የአማራ ክልል ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ የካይዘን ፍልስፍናን ተግባራዊ ማድረጉ የስራ ጥራትና ቅልጥፍና መኖሩን  ገልጸው ሌሎች ተቋማትም ልምድ ሊወስዱበት እንደሚገባ ተናግረዋል። በሌላ በኩል  የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት፣ ሰላምና ደህንነት ቢሮ እና ፖሊስ ኮሚሽን ደንበኞችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ምቹ የስራ ቦታ አለመኖሩን ገልፀዋል። ጉብኝቱም  የስራ ቦታ ጥበትና  መሰል ችግሮችን በመገንዘብ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማዘጋጀት ያለመ በመሆኑ በቀጣይ የተቋማቱን ችግር ለመፍታት እንደሚሰራ አስታውቀዋል። በተለይ የክልሉ ሰላምና ደህንነት ቢሮና ፖሊስ ኮሚሽን እያንዳንዳቸው ግዙፍ ተቋማት ሁነው እያለ በአንድ ተቋም ስር ስራቸውን እንዲያከናውኑ መደረጉ ከፍተኛ የስራ ጫና መፍጠሩን አመልክተዋል። ተቋማቱ የየራሳቸው ህንጻ እንዲኖራቸው ለማድረግም የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል። በየተቋማቱ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመለየትትና ችግሩን ለመፍታት የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ  ተልኮ ተሰጥቶት ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ችግሩን ከለየ በኋላ ለአገልግሎት አሰጣጥ ማነቆ የሆኑ የህግም ሆነ የአደረጃጀት ችግሮች በጥናቱ መሰረት የሚሻሻሉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። የአማራ ክልል ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን  ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መብት አድማስ በበኩላቸው የርዕሰ መስተዳደሩ ደንገተኛ ጉብኝት ሰራተኛው ስራውን በሃላፊነትና ሁሌም ዝግጁ እንዲሆን ያነሳሳል ብለዋል። በተጨማሪም ችግሮችን በቅርበት ተረድተው ለመፍትሄው አቅጣጫ እንዲቀመጥ ያግዛል ብለዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ መሰል የተቋማት ጉብኝት ከዚህ በፊት ማከናወናቸውም ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም