አትሌት ብርሃኔ ዲባባ በኮፐንሀገን የግማሽ ማራቶን ውድድር አሸነፈች

97
መስከረም 4/2012 አትሌት ብርሃኔ ዲባባ ዛሬ በዴንማርክ የኮፐንሀገን ግማሽ ማራቶን ውድድር በአንደኝነት ስታሸንፍ ፤ በኬፕታውን ማራቶን ደግሞ ኑሪት ሽመልስና ጌጤ መንዳ 2ኛ እና 3ኛ ወጥተዋል። አትሌት ብርሃኔ ውድድሩን 1 ሠዓት ከ5 ደቂቃ ከ57 ሴኮንድ በመግባት ስታሸነፍ በርቀቱም የግል ምርጥ ሠዓቷን በ1 ደቂቃ ከ50 ሴኮንድ አሻሽላለች። የ26 ዓመቷ አትሌት የርቀቱ የግል ምርጥ ሠዓቷ የነበረው እ.አ.አ 2016 በቻይና በተካሄደው የያንግዡ ግማሽ ማራቶን 1 ሠዓት ከ7 ደቂቃ ከ17 ሴኮንድ በመግባት ያስመዘገበችው ነው። እ.አ.አ በ2010 በሶስት ሺህ ሜትር ሩጫ ወደ አትሌቲክሱ የገባችው ብርሃኔ ዲባባ ከአራት ዓመት በፊት ወደ ጎዳና ሩጫ በመግባት በዓለም አቀፍ ውድድሮች በመሳተፍ ላይ ትገኛለች። እ.አ.አ በ2015 እና 2018 የቶኪዮ ማራቶን ማሸነፍ ችላለች። በዛሬው ውድድር ኬንያዊቷ አትሌት ኢቫሊን ቺርቺር 1 ሠዓት ከ6 ደቂቃ ከ22 ሴኮንድ በመግባት 2ኛ ስትወጣ ሌላዋ አትሌት ዶርካስ ጄፕቺርቺር በ1 ሠዓት ከ6 ደቂቃ ከ36 ሴኮንድ 3ኛ ሆና አጠናቃለች። በወንዶች ኬንያዊው አትሌት ጂኦፍሬይ ካምዎሮር የግማሽ ማራቶንን የዓለም ክብረ ወሰን መስበር ችሏል። የ26 ዓመቱ አትሌት 58 ደቂቃ ከ1 ሴኮንድ በመግባት ባለፈው ዓመት በስፔን በተካሄደው የቫሌንሺያ የግማሸ ማራቶን ውድድር በኬንያዊ አትሌት አብርሃም ኪፕቱም ተይዞ የነበረውን የርቀቱን ክብረ ወሰን በ17 ሴኮንድ አሻሽሏል። ጂኦፍሬይ ካምዎሮር የዓለም ክብረ ወሰን ቢሰብርም የክብረ ወሰን ባለቤትነቱ የሚጸድቀው የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአበረታች መድሐኒት የምርመራ ውጤትና የመወዳደሪያ ስፍራው ደረጃውን የጠበቀ ነው የሚለውን ካጣራ በኋላ ነው። ይህ አትሌት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባስመዘገባቸው ውጤቶች በግማሽ ማራቶን ውድድር ስሙ በቀዳሚነት የሚነሳ ነው። ሌላው ኬንያዊ በርናርድ ኪፕኮሪር ንጌኖ 59 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ በመግባት 2ኛ ሲወጣ አትሌት ብርሃኑ ጽጉ 59 ደቂቃ ከ22 ሴኮንድ በመጨረስ 3ኛ ደረጃን ይዟል። በሌላ በኩል ዛሬ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የኬፕ ታውን ማራቶን ሴቶች ኬንያዊቷ አትሌት ሴሊስቲን ቼፕቺርቺር በ2 ሠዓት ከ26 ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ አሸናፊ ስትሆን በናሚቢዊቷ አትሌት ሄላሊያ ጆሀንስ የተያዘውን የቦታውን ክብረ ወሰን በ2 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ አሻሽላለች። አትሌት ኑሪት ሽመልስ 2 ሠዓት ከ27 ደቂቃ ከ40 ሴኮንድ ሁለተኛ ስትወጣ አትሌት ጌጤ መንዳ 2 ሠዓት ከ28 ደቂቃ ከ32 ሴኮንድ ሶስተኛ ሆናለቸ። በወንዶች ኬንያዊያኖቹ አትሌቶች ኤድዊን ኮኤችና ዳንኤል ሙቴቲ አንደኛና ሁለተኛ ሲወጡ ሞሮኮዋዊው አትሌት መሐመድ ዚያኒ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም