ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ዛሬ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ይሳተፋሉ

142
አዲስ አበባ መስከረም 4/2012 ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ዛሬ በዴንማርክ ኮፐንሀገንና በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶንና የማራቶን ውድድሮች ይሳተፋሉ። በአምስተኛው የዴንማርክ ኮፐንሀገን የግማሽ ማራቶን ዛሬ በሴቶች አትሌቶቹ ገነት ያለውና ድባቤ ኩማ ይሳተፋሉ። በ3፣ በ5 እና በ10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ሩጫ የጀመረችው አትሌት ገነት ያለው ላለፉት ሶሰት ዓመታት በዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶንና የማራቶን ውድድሮች በመሳተፍ ላይ ትገኛለች። እ.አ.አ በ2016 በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በተካሄደው የራስ አል ካይማህ የግማሽ ማራቶን ውድድር 1 ሠዓት ከ6 ደቂቃ ከ26 ሴኮንድ በመግባት በርቀቱ የግል ምርጥ ሠዓቷን ማስመዝገብ ችላለች። አትሌት ገነት በሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም በጀርመን በተካሄደው የሀምቡርግ ማራቶንም አሸንፋለች። ሌላዋ የውድድሩ ተሳታፊ አትሌት ድባቤ ኩማ ባለፈው ዓመት የጎዳና ላይ ሩጫን ተቀላቅላ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውደድሮች ላይ በመሳተፍ ላይ ነች። በየካቲት ወር 2011 ዓ.ም በስፔን ባርሴሎና ግማሽ ማራቶን 1 ሠዓት ከ6 ደቂቃ ከ45 ሴኮንድ በመግባት በርቀቱ የግል ምርጥ ሠዓቷን አስመዝግባለች። በዛሬው የኮፐንሃገን ውድድር ኬንያዊያን አትሌቶች የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት እንደተሰጣቸው የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስፍሯል። በወንዶች ውድድር አትሌት ታዱ አባተ ይሳተፋል። አትሌት ታዱ እ.አ.አ 2017 በፓርቹጋል የሊዝበን የግማሽ ማራቶን 1 ሠዓት ከ00 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ በመግባት በርቀቱ የግል ምርጥ ሠዓት ማስመዝገቡ ይታወሳል። የ22 ዓመቱ አትሌት ባለፈው ዓመት መጨረሻ በጀርመን ሀምቡርግ የግማሽ ማራቶንም አሸናፊ ነበር። እንደ ሴቶቹ ውድድር በወንዶቹም ኬንያዊያን አትሌቶች የማሸነፍ ቅድሚያ ግምቱን ያገኙ ሲሆን አትሌት ጂኦፍሬይ ካምዎሮር ውድድሩን በአሸናፊነት ያጠናቅቃል ተብሎለታል። የኮፐንሀገን የግማሽ ማራቶን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ነው። ባለፈው ዓመት ውድድር በሴቶች በትውልድ ኢትዮጵያዊት በዜግነት ኔዘርላንዳዊት የሆነቸው አትሌት ሲፋን ሀሰን፤ በወንዶች ኬንያዊው አትሌት ዳንኤል ኪፕቹምባ አሸናፊዎች ነበሩ። በሌላ በኩል ዛሬ በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የኬፕ ታውን ማራቶን በሴቶች አበባ ገብረመስቀልና ኡርጌ ዲሮ ይሳተፋሉ። አትሌት አበባ ባለፈው ዓመት በስፔን የሲቪያ ማራቶን 2 ሠዓት ከ24 ደቂቃ ከ53 ሴኮንድ በመግባት ውድድሩን ስታሸንፍ የገባችበት ጊዜ የርቀቱ የግል ምርጥ ሠዓቷ ነበር። አትሌት ኡርጌም ባለፈው ዓመቱ የሲቪያ ማራቶን አበባን ተከትላ ሁለተኛ ሰትወጣ 2 ዓት ከ28 ደቂቃ ከ10 ሴኮንድ የርቀቱ የግል የምርጥ ሠዓቷ ነው። በወንዶች ውድድር የሚሳተፈው አትሌት አብዲ ፉፋ ባለፈው ዓመት በቻይና ሻንጋይ ማራቶን 2 ሠዓት ከ9 ደቂቃ ከ24 ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሠዓት ያስመዘገበበት ነው። በሁለቱም ጾታዎች በሚካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ወድድሩን እንደሚያሸንፉ ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል እንደሚገኙበትና ከደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ አትሌቶች ጠንካራ ፉክክር እንደሚጠብቃቸውም ተገልጿል። ለ13ኛ ጊዜ የሚካሄደው የኬፕ ታውን ማራቶን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ ያለው ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም