የማዕድን ዘርፍ በመንግስት በኩል እየተደረገለት ያለው ድጋፍና የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው -የዘርፉ ተዋናዮች

98
መስከረም 3/2012 የማዕድን ዘርፍ በመንግስት በኩል እየተደረገለት ያለው ድጋፍና የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ገለጹ። መንግስት በበኩሉ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው መስኮች አንዱ የማዕድን ዘርፍ ይሆናል ብሏል። በአምባሳደር ግርማ ብሩ የሚመራ የጠቅላይ ሚኒስቴር የኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ በማዕድን ዘርፉ የኤክስፖርት አፈጻጸም ላይ ያሉ ማነቆዎች እንዲፈቱ ለማድረግ ከማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አድርገዋል። ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ ዋና ዋና ማዕድናት የምርት አቅርቦትና ግብይት ላይ ያሉ መሰረታዊ ችግሮች፣ የመፍትሔ አቅጫዎች እና የባለድርሻ አካላት ሚና በሚል በማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል። የዘርፉ ተዋናዮች መንግስት እያደረገ ያለው ድጋፍ፣ ክትትልና ዘርፉ ካለው እምቅ አቅምና ከሚያስገኘው ገቢ አንጻር በመረዳት የሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑን በመድረኩ ላይ አንስተዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ያለው የህገ ወጥ የማዕድን ምርቶች ንግድ በህጋዊ መንገድ የሚሰሩ አካላት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንና መንግስትም የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። በተደጋጋሚ በማዕድኑ ዘርፍ ስላሉ ችግሮች ውይይት ይደረጋል ችግሮቹም በስፋት ይነሳሉ የሚመለከታቸው አካላትም በጉዳዩ ላይ መፍትሄ በመስጠት እርምጃ ሲወስዱ ግን አይታይም ነው ያሉት የዘርፉ ተዋናዮች። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማይክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ መንግስት ከዚህ በፊት ትኩረት ያልተሰጠውን የማዕድኑን ዘርፍ ትኩረት እንዲያገኝ ወስኗል ብለዋል። ከህገ ወጥ ማዕድን ምርትና ሽያጭ በተለይም ከወርቅ ግብይት አንጻር የተነሱ ሀሳቦችን በጥልቀት የችግሩን ምንጭ መተንተን እንደሚያስፈልግና በዚህም ረገድ አስፈላጊው ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል። በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በኩል የማዕድን ዘርፉን ችግሮች መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሚሰራ አምስት አባላት ያሉት ግብረ ሃይል መቋቋሙንም ገልጸዋል። የተነሰቱን ችግሮች በዝርዝር በኮሚቴው ጥልቅ ውይይት እንደሚካሄድባቸውና ከፖሊሲና ከአሰራር አኳያ እንዲሁም መንግስት ምን አይነት ድጋፍ ማድረግ አለበት? በሚለው ዙሪያ ዝርዝር የመፍትሄ ሀሰቦች እንደሚቀርቡም አመልክተዋል። መንግስት ከአራት እስከ ስድስት ወር ባለ ጊዜ በባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ እንዲሁም የተቋቋመው ግብረ ሃይል እየተገናኘ ምክክሮችን በማድረግ አቅጣጫና መፍትሄ እንደሚሰጥም ገልጸዋል። ማዕድን ከማውጣት እስከ መላክ ያሉ ውስብስብ ማነቆዎችን ለመፍታት የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያሻም አክለዋል። በማዕድን ዘርፍ ያሉ የኤክስፖርት ማነቆዎችን አስመልክቶ በቀረበው መነሻ ጽሁፍ ላይ በዘርፉ የቴክኖሎጂ አቅርቦት ዝቅተኛ መሆን፣ ለአምራቾች የሚደረገው የፋይናነስ፣ የቴክኒክና የአቅም ግንባታ ድጋፍ አነስተኛ መሆን፣ በዘርፉ ያለው የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ደካማ መሆኑ የዘርፉ ዋነኛ ማነቆዎች እንደሆኑ ተገልጿል። ህገወጥ የማዕድን ምርቶች በተለይም የወርቅ ንግድ መስፋፋት፣ ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ አለመላክ፣ መንግስት በዘርፉ የሚሰጠውን ድጋፍና ማበረታቻ ተግባራዊ አለማድረጉ ሌሎች የተነሱ ችግሮች ናቸው። የማዕድን ዘርፉ የቅንጅት አሰራር ማጠናከር፣ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ማድረግ፣ ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ መላክ፣ ህገ ወጥ ግይትን ለመከላከል ኮማንድ ፖስቶችን ማቋቋምና እሴት መጨመር ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት በመፍትሄነት ቀርቧል። በርካታ የሚባሉ የዘርፉ ችግሮችና ማነቆዎች ተነስተው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል። የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የክልል ማዕድን ልማት ኤጀንሲና ጽህፈት ቤቶች የተነሱትን ችግሮች ለመፍታት የጀመሯቸው ስራዎች እንዳሉ ሆነው በቀጣይ በችግሮች ላይ መፍትሄ ለመስጠት በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በ2012 ዓ.ም ከማዕድን ዘርፍ 265 ሚሊዮን ዶላር የኤክስፖርት ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም