ኢህአዴግ አሁን ባለበት ቁመና አይቀጥልም -ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

80
አዲስ አበባ መስከረም  3/2012  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አሁን ባለበት ቁመና እንደማይቀጥል ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ጋር በነበራቸው የቅዳሜ ጨዋታ ፕሮግራም በወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል። በንግግራቸው ኢህአዴግ አሁን ያለውን አደረጃጀት ለመቀየር የተለያዩ ውይይቶችን ማድረጉን ጠቅሰው በቀጣይም አሁን ያለበትን ቁመና ይቀይራል ብለዋል። የገዢው ፓርቲ የአደረጃጀት ለውጥን አስመልክቶ አሁን ላይ ሆኖ መልኩና ቅርጹ ይሄ ይሆናል ማለት ግን አያስችልም ነው ያሉት። የፓርቲውን ቁመና እንዴት መቀየር ይቻላል? ይሄ መቼ ይሆናል? መቼ ይጀመራል? በምን አይነት መልኩ? የሚሉት ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተደረገ መሆኑንና ፓርቲው የደረሰብትንም ነገር በቅርብ ያሳውቃል ብለዋልል። ምርጫን በተመለከተም በቀጣዩ ብሄራዊ ምርጫ ሊከሰቱ የሚችሉ ፈተናዎችን እንዴት አድርጎ ማስቀረትና ማለፍ እንደሚቻል ማሰብ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያንም በዚህ ላይ ሰፊ ተሞክሮ አላቸው ብለዋል። ምርጫ ሲካሄድ የምርጫ ውጤትን ተቀብሎ ዝም ብሎ ማለፍና በ1997 ዓ.ም በነበረው ምርጫ ዜጎች መስዋዕትነት ከፍለው ሊመጣ የነበረውን አደገኛ ነገር ማስቀረት መቻላቸው እንደ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልም ተናግረዋል። ምርጫው ይራዘም የሚሉት የሚያቀርቡት ሀሳብ ምክንያታዊ እንደሆነና አይራዘም የሚሉትም ህጋዊ መሰረት እንዳላቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫው ለሁለት ለሶስት ዓመት ቢራዘም በተራዘመው ዓመታት ውስጥ የሚባሉትን ችግሮች መፍታት ይቻላል ወይ የሚለውን ጉዳይ በትኩረት መመልከት ያስፈልጋል ብለዋል። ለምርጫ ውጤታማነት ጋዜጠኛው፣ የሙያ ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል። መንግስት ምርጫው ዴሞክራያዊ፣ ፍትሐዊ፣ነጻና ገለልተኛ እንዲሆን እየሰራ መሆኑንና ገዢው ፓርቲ ካሸነፈ ህዝቡ የጣለበትን ሃላፊነት መወጣት እንደሚቀጥልና ከተሸነፈም ስልጣኑን እንደሚያስረክብም አረጋግጠዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ሲያነሷቸው ከነበሩ ሀሳቦች በመውጣት ህዝቡን የሚጠቅም የተደራጀ ሀሳብና እቅድ አዘጋጅተው ለምርጫው ፉክክሩ መቅረብ አለባቸውም ብለዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም