በዞኑ ለ98 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ

51
መስከረም 3/2012 በትግራይ ምእራባዊ ዞን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ጥያቄ ላቀረቡ 98 ባለሃብቶች ፈቃድ መስጠቱን የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ሚዛን ታደሰ ለኢዜአ እንደገለፁት ከሐምሌ 1 ቀን 2010 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሃብቶቹ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ባለሃብቶቹ ከሚሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት ኘሮጀክቶች መካከል ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽንና የአገልግሎት ዘርፍ ይገኝበታል፡፡ የታቀዱ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁም 9 ሺህ 500 ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል እንደሚፈጥሩ አስታውቀዋል፡፡ በዞኑ በ2010 በጀት ዓመት 93 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ሚዛን ያስመዘገቡት ካፒታል መጠን ግን 307 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደነበር ገልጸዋል። በዞኑ ሰፊ ድንግል የእርሻ መሬት፣ የተሻለ መረጋጋትና በመገንባት ላይ ያሉ ሁለት ትላልቅ የኢንዱሰትሪ ፓርኮች መኖር ለኢንቨስትመንቱ ፍሰት መጨመር በጎ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል። የባለሃብቶቹ ካፒታል ፍሰት ተከትሎም በርካታ የአከባቢው ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ቀደም ሲል የዞኑ የኢንቨስትመንት መስኮች በሰሊጥ፣ ማሽላና ጥጥ የግብርና ምርቶች በማምረት ላይ ተወስኖ መቆየቱን አስታውሰው ዛሬ ላይ ወደ ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽንና ወደ ተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ እየተስፋፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሁመራ ከተማ ከትንሽ የንግድ ተቋም ተነስቶ ዛሬ ላይ በ11 ሚለዮን 400 ሺህ ብር ወጪ ዘመናዊ ሆቴል በመገንባት የተሰማራው ወጣት ባለሃብት ተወልደ አማረ እንዳለው፣ የዞኑ መስተዳደር በፈጠረው አዲስ የኢንቨስትመንት እድል ተጠቃሚ ሊሆን መቻሉን ተናግረዋል። በዘርፉ ያለው እንቅስቃሴም ከቀድሞ የተሻለ መሆኑን ያመለከተው ወጣት ባለሃብቱ፣ በመሰረተ ልማት የሚታዩ ክፍተቶች ግን ከወዲሁ መስተካከል እንደሚገባቸው አሳስቧል። በኬሚካል ማኒፋክቸሪንግ ሽርክና ማሕበር የተሰማሩ ሃፍቶም ገብረእግዛብሄር እና ሙለይ በርሀ በጋራ በሰጡት አስተያየት በጋራ ባቋቋሙት የፈሳሽ ሳሙና ፋብሪካ በየቀኑ 300 ሊትር እያመረቱ ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። ሁለት ዓመት ያልሞላው ፋብሪካቸው ከ800 ሺህ ብር በላይ ተንቀሳቃሽ ካፒታል ያፈራ ሲሆን ለ15 ሰዎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም