በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተተከሉ ችግኞች ክብካቤ እየተደረገላቸው ነው

62
መስከረም  3/2012 በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ባለፈው አመት ቃጠሎ በደረሰበት አካባቢ የተተከሉ ችግኞች በህብተሰቡ ተሳትፎ የመከባከብና የመጠበቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡ ''ፓርኩየህልውናችንመሰረትበመሆኑአስፈላጊውንጥበቃናክብካቤእያደረግንነው''ሲሉነዋሪዎችገልፀዋል። የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፈው የበጋ ወቅት በተከሰተ የእሳት ቃጠሎ በፖርኩ ደን ላይ የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመተካት እየተሰራ ይገኛል። በቃጠሎ ጉዳት የደረሰበት አካባቢ መልሶ እንዲያገገም ለማድረግም በዘንድሮው የክረምት ወቅት ህብረተሰቡን በማስተባበር ከ38ሺ በላይ ለአካባቢው ስነ ምህዳር የተመረጡ ሀገር በቀል ዛፎች መተከላቸውን ተናግረዋል። በእሜት ጎጎ እና ሳንቃ በር በተባሉት የፓርኩ አካባቢዎች የተተከሉትን ችግኞች የፓርኩ ስካወቶች፣ የኢኮ ቱሪዝም ማህበራትና የደባርቅ ከተማ ወጣቶች ጥብቃና ክብካቤ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የኩትኳቶ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ አብዛኛው ችግኝ በጥሩ ሁኔታ የጸድቀት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ በፓርኩ አካባቢ ቱሪስቶችን በማስጎብኘት ስራ ላይ የተሰማራው ወጣት ሰለሞን ጫኔ በበኩሉ በፓርኩ ላይ አምና በደረሰው ቃጠሎ ማዘናቸውን ገልጿል፡፡ በህብረተሰቡና በመንግስት ትብብር ቃጠሎው በቁጥጥር ስር ውሎ መልሶ እንዲያገገም ችግኝ ከመትከል ጀምሮ የተተከሉ ችግኞችን በመከባከብ ወጣቶች ሰፊ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በደባርቅ ከተማ የሚገኘው የቱሪዝም ልማትና ግብይት ህብረት ስራ ማህበር ሊቀ መንበር ቄስ ሞገስ አየነው በበኩላቸው ከ7ሺ በላይ የሚሆኑት የማህበሩ አባላት በፓርኩ ጥበቃና ልማት ስራ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው አመት በፓርኩ የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር በተደረገው ርብርብ የማህበሩ አባላት እገዛ ከፍተኛ ነበር ያሉት ሊቀ-መንበሩ በያዝነው ክረምትም የተተከሉ ችግኞችን አባላቱ እየተንከባከቡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ ባለፈው አመት በፓርኩ ላይ በደረሰው የሁለት ጊዜ የእሳት ቃጠሎ 1ሺ 40 ሄክታር በሚሸፍን የጓሳ ሳርና የቁጥቋጦ ዛፍ ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1978 በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡ ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የበርካታ ብርቅዬ አእዋፋትና የዱር እንስሳት መገኛ ስፍራም ነው፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም