የዘንድሮው የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት እንቁጣጣሽ በዓል በኬንያዋ የወደብ ከተማ ሞምባሳ ሊከበር ነው

128
መስከረም 2/2012 የዘንድሮው የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት እንቁጣጣሽ በዓል በመጪው እሁድ መስከረም 4 ቀን 2012 ዓም በኬንያዋ የወደብ ከተማ ሞምባሳ በደማቅ ስነ-ስርዓት እንደሚከበር በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ። በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሞምባሳ ከሚገኘው ሼባ ላውንጅ ጋር በመተባበር በክብረ በዓሉ ላይ የተለያዩ የኢትዮጵያ ባህሎች እና ትውፊቶችን የሚያንፀባርቁ ትእይንቶችን ያቀርባሉ። የኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎችም በተንቀሳቃሽ ምስል ለዕይታ ይቀርባሉ ተብሏል። ከክብረ በዓሉ ጎን ለጎንም በሞምባሳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ባለኃብቶች ጋር በሀገራቸው ሀብት እና እውቀታቸውን ፈሰስ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚካሄድም ኤምባሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። ከተለያዩ አስጎብኚ ድርጅቶች እና የጉዞ ወኪሎች ጋርም የኢትዮጵያን ቱሪስት መስህቦች ለኬንያውያን ለማስተዋወቅና ተደራሽ ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ምክክር ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም