በአፋር የበረሃ አንበጣን የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

136
መስከረም 2/2012 በአፋር ክልሉ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ ባለፉት ሁለት ሳምንታት አንበጣው በነበረበት  ከ4ሺህ446 ሄክታር መሬት ላይ  በሰውና በሄሌኮፍተር  የታገዘ የመድኃኒት ርጭት ተካሂዷል። በሚኒስቴሩ የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የተዛማች እጽዋት በሽታ መከላከል ኬዝቲም አስተባበሪ አቶ በላይ ፈንታነው እንዳሉት  ከሰኔ 2011ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ከየመን ወደ አፋር የገባውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከል  ከክልሉ ጋር በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ። አንበጣው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ቢከሰትም በዋናነት  በአውሲ-ረሱ ዞን ጭፍራ፣ አደአር እና ሚሌ ወረዳዎች  በስፋት እንደሚገኝ በተደረጉ ቅኝቶች መረጋገጡን አመልክተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች በሰው ኃይል ለመከላከል ጥረቱ ቢኖርም  ስፋትያለ መንጋ በመሆኑ ከነሐሴ 2011 ዓ.ም  መጨረሻ ሳምንት ጀምሮ በሄሌኮፍተር በመታገዝ የመድኃኒት ርጭቱ እንደቀጠለ ነው። እስካሁንም   600 ሊትር ኬሚካል በመጠቀም ከ4ሺህ 446 ሄክታር በላይ መሬት  መረጨቱን አስተባባሪው አመልክተዋል። ርጭቱ  ከተካሄደባቸው  ወረዳዎች ውስጥ በተለይ  ከፍተኛ የአምበጣ መንጋ እንቅስቃሴ በሚታይበት የጭፍራ አካባቢ መሆኑን ጠቁመዋል። አንበጣው ከአፋር አማራ ከልል አጎራባች ወረዳዎች እየገባ እንደሆነ ያመለከቱት አስተባባሪው  ህብረተሰቡና በየደረጃው  የሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት  የመከላከል ስራ በማገዝ ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል። የበረሃ አንበጣው ሳይስፋፋ ለመቆጣጠር የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል። በአፋር ክልል እንስሳት፣ ግብርናናና  ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የእጽዋት ጤና ጥበቃ ባለሙያ አቶ አሊመሃመድ በበኩላቸው የበረሃ አንበጣው  በክልሉ በ16ወረዳዎች መከሰቱን ገልጸዋል። መንጋ የሆነው አንበጣው  የአርብቶ አደሩ የኑሮ መሰረት የሆነው  የእንስሳት መኖ እየጎዳ መሆኑን አመልክተዋል። እንደባለሙያው ገለጻ ሀብረተሰቡአንበጣው  ሊደርስ የሚችውን ጉዳት በቂ ግንዛቤ ኖሮት  የመከላከል ስራውን በባለቤትነት እንዲሳተፍ ከወረዳና ቀበሌ አመራሮች እንዲሁም የግብርና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን  በማሰተባበር የንቅናቄ ስራ እየተካሄደ ነው። ህብረተሰቡ  የሚታወቅበትን  “ዳጉ” የተባለው የአፋር  ባህላዊ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት  በአግባቡ  በመጠቀም ባህላዊ  የመከላከል ስራው በመተጋገዝ እንዲቀጥልም  ጥሪ አቅርበዋል። በባህላዊ የመረጃ ለውውጡ ህብረተሰቡ አንበጣው ያረፈበትን በመጠቆም የሚያግዝበት ዘዴ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም