በኢትዮጵያ የሳንባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት የሚያስችል ስምምነት በአሜሪካና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል ተደረገ

56
መስከረም 2 ቀን 2012 በኢትዮጵያ የሳንባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት የሚያግዙ ተግባራትን በጋራ ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት በኢትዮጵያና አሜሪካ መንግስታት መካከል ተደረገ። ስምምነቱን የፈረሙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሊያ ታደሰና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ (ዩ ኤስ ኤይድ) ልዑክ ዳይሬክተር ሚስተር ሲን ጆንስ ናቸው። በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ የሳንባ በሽታን ከዓለም ለማጥፋት እንዲቻል በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ አማካኝነት በሚተገበረውና በ30 አገራት ላይ የሚያተኩረው የሳንባ በሽታ መከላከል መርሃ ግብር አካል ትሆናለች። መርሃ ግብሩ  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ እስከ 2022  ድረስ በአለም አቀፍ ደረጃ 40 ሚሊዬን የሚደርስ የሳንባ በሽታ ህመምተኛን ለመርዳት የያዘውን ትልም ማሳካት ይችል ዘንድ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ (ዩ ኤስ ኤይድ) በራሱ በኩል የተለያዩ ተባባሪዎቹን በማስተባበርና ኃብት በማሰባሰብ የዘየደው ስልት ነው። የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ካለፉት 19 ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ የሳንባ በሽታን ለመከላከያ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከር ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል። በዚህም እስካሁን ከ2 ሚሊዬን በላይ የሚሆኑ የሳንባ በሽታ ተጎጂዎችን በመለየት ህክምና መስጠት መቻሉን በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። ይህም በባለፉት ሁለት አስርት አመታት ውስጥ የህመሙን ክስተት በግማሽ፤ ከህመሙ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን ሞት ደግሞ 70 በመቶ እንዲቀንስ አግዟል። የአሜሪካ መንግስት በየአመቱ  150 ሚሊየን ዶላር በመመደብ  የሳንባን ፣ ኤች..አይ.ቪ/ኤድስን፣ ወባንና ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል እንዲሁም የእናቶችና ህጻናትን ጤናን ለማሻሻል የሚያስችል ድጋፍ በማቅረብ የኢትዮጵያ ዋነኛ አጋር ነው ሲልም መግለጫው ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም