በዞኖቹ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ከ100ሺህ በላይ ህጻናት ተመዘገቡ

56
ነገሌ /ነቀምት ኢዜአ መስከረም 2 ቀን 2012 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ፣ ቄለምና ሆሮጉድሩ ወለጋ ዞኖች በተያዘው የትምህርት ዘመን እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት ሁሉ ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት ምዝገባ መካሄዱን የየዞኑቹ ትምህርት ፅህፈት ቤቶች አስታወቁ። በዞኖቹ ከ100 ሺህ በላይ  ህፃናት መመዝገባቸው ተመልክቷል። የጉጂ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጋሽ ቡላላ ለኢዜአ እንደገለፁት ባለፉት ሁለት ወራት ቤት ለቤት በተካሄደ አሰሳ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ 71 ሺህ 226 ህጻናት ተመዝግበዋል ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት ለማሳደግ በህብረተሰቡ ተሳትፎ 12 መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ ተደርገዋል። ትምህርት ቤቶቹ እያንዳንዳቸው 48 የመማሪያ ክፍሎችና የአስተዳደር ቢሮዎች ያሏቸው ናቸው። በተያዘው ወር ለሚጀመረው የመደበኛ ትምህርት መርሀ ግብር ከ200 ሺህ በላይ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል። "በመደበኛ መርሀ ግብር የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት በ73 ሺህ ብልጫ አለው" ብለዋል ። እንደ ኃላፊው ገለጻ በትምህርት ዘመኑ አዲሶቹን ጨምሮ በ866 መደበኛ ትምህርት ቤቶችና 8ሺህ መምህራን የመማር ማስተማር ስራው ይካሄዳል ። በተመሳሳይ በቄለም ወለጋ ዞን እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ 20 ሺህ768 ሕፃናት መመዝገባቸውን የዞኑ የትምህርት ጽህፈት ቤት አስታውቋል። የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኬኔሣ ቀልቤሳ እንደገለፁት ምዝገባው የተካሄደው በዞኑ 11 ወረዳዎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ነው ። ከተመዘገቡት ሕፃናት መካከል10ሺህ 187 ሴቶች ናቸው። በትምህርት ዘመኑ የተማሪዎች መጨናነቅን ለማቃለል በህብረተሰቡ ተሳትፎ በ29 ሚሊዮን ብር 127 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ተገንበተው ለአገልግሎት ተዘጋጅተዋል። እንደ ሰራ አስኪያጁ ገለጻ 2ሺህ623 አዲስ የተማሪ መቀመጫዎችም እንዲሟሉ ተደርጋል ። በዞኑ በትምህርት ዘመኑ በአንደኛና  ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን የሚከታተሉ 126 ሺህ 233 ነባርና አዲስ  ተማሪዎች ተመዝገበዋል ። የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የትምህርት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ንጉሴ ረጋሣ በበኩላቸው እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ 9ሺህ 627 ህጻናት መመዝገባቸውን ገልጸዋል። በዞኑ በሚገኙ 370 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች 223ሺህ 684 ተማሪዎች መመዝገባቸውን አስታውቀዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም