በዘመኑ የአካባቢውን ህብረተሰቡን የልማት ችግሮች ለማቃለል በትኩረት እንደሚሰራ የነገሌ ከተማ አስተዳደር ገለጸ

58
መስከረም 2/2012 በተያዘው አዲስ ዓመት የአካባቢውን ህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለማቃለል በትኩረት እንደሚሰራ የነገሌ ከተማ አስተዳደር ገለጸ። የከተማው አስተዳደር ምክር ቤት ጉባኤ በነገሌ የተካሄደ ሲሆን ለስራ ዘመኑ ማስፈጸሚያም  ከ81 ሚሊዮን  ብር በላይ በጀት አጽድቋል፡፡ በዚህ ወቅት የከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አብዱረዛቅ ሁሴን እንዳሉት የትምህርት፣የመጠጥ ውሀ፣ ሌሎች  የመሰረተ ልማት ችግሮችና ጉድለቶች ተለይተዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ማለቅ ለሚገባው ጉዳይ ቀጠሮ በመስጠት ተገልጋዮች የሚጉላሉበት የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ "ችግሮቹን ለማቃለል በተያዘው አዲስ ዓመት  የአመራር ክህሎት ስልጠና ፣ የበጀት ድልድና የአዳዲስ መሰረተ ልማት ማስፋፊያና ግንባታ ስራዎች ይከናወናሉ "ብለዋል፡፡ ከሚከናወነው ልማት ውስጥም ስምንት የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ትምህርት ቤት፣ ሶስተ  ኪሎ ሜትር የአስፋልትና የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታ ይገኙበታል፡፡ በከተማው ውስጥ ባለፈው ዓመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችም ፍጻሚያቸው እንዲያገኙ ይደረጋል። ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር የሚያግዙ ዘጠኝ የመስሪያና የመሸጫ ግንባታ ለመጀመር የሚያስችል የቦታ መረጣ ስራ መጠናቀቁን ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል። ምክር ቤቱ ካጸደቀው በጀት 55 ሚለዮን 718 ሺ ከክልሉ መንግስት ቀሪው ደግሞ በከተማ አስተዳደሩ ገቢ የሚሸፈን መሆኑም ተገልጿል፡፡ ከበጀት ውስጥ ለልማት ስራዎች ማከናወኛ መያዙም ምክትል ከንቲባው  አመልክተው ሌሎችም የህብረተሰቡን ችግች ለማቃለል በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል። ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ሻለቃ መታ ሞሉ በቃል በሰጡት አስተያየት በአከባቢው የመጠጥ ውሀና ሌላም የመሰረተ ልማት  ችግር እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ይህን ችግር ለማቃለል በዘመኑ ይከናወናል የተባለው ስራ እውን ሆኖ  በተግባር ማየት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ሌላው ነዋሪ አቶ አሰፋ ጃለታ በበኩላቸው  አመራሩ እቅዱን ለማሳካት ከህብረተሰቡ  ጋር ተወያይቶና ተባብሮ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም