በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ዝናብ ይጥላል - የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ

119
መስከረም 2/2012 በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እንደሚጠበቅ የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ። የክረምት ዝናብ ሰጪ የሜቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በተለይም በአገሪቱ ሰሜንና ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች እየተዳከመ እንደሚመጣ የሚጠበቅ ቢሆንም በመጪዎቹ አስር ቀናት ግን በርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ዝናብ ይኖራቸዋል ሲል ኤጀንሲው አመልክቷል። በዚህ መሰረት ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሊባቡር፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ አዲስ አበባ፣ አማራ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ አዊ ዞንና የሰሜን ሸዋ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህም ሌላ አብዛኛው የትግራይ ክልል ዞኖች፣ የጋምቤላና የቤንሻንጉል ዞኖች፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የከፋ፣ የቤንቺ ማጂ፣ የጉራጌ፣ የሐዲያ፣ የወላይታ፣ የዳውሮ፣ የጋሞ ጎፋ፣ የሲዳማ ዞኖችም በተመሳሳይ ዝናብ ይኖራቸዋል። የሚጠበቀው ዝናብ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ለቅጽበታዊ ጎርፍ መከሰት መንስኤ ሊሆን ይችላል ሲልም ኤጀንሲው አመልክቷል። በሌላ በኩል የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የአፋረ ዞን 3፣ 4 እና 5፣  እንደዚሁም ምዕራብና ምስራቅ ቦረና፣ ድሬዳዋና ሐረረ፣ የአርሲና ባሌ ዞኖች፣ የደቡብ ኦሞ፣ የሰገን ህዝቦች እንዲሁም የደጋሃቡር፣ የጅጅጋና የሽንሌ ዞኖች አንዳንድ ስፍራዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል። የተቀሩት የአገሪቱ አካባቢዎች በአብዛኛው ደረቅ ሆነው እንደሚሰነብቱ ነው ኤጀንሲው በመግለጫው የጠቆመው። የሚጠበቀው ዝናብ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ላለው የግብረናው ሥራ ገንቢ ሚና ይኖራቸዋል። በመሆኑም ዝናቡ ቀደም ብለው ለተዘሩና ፍሬ በመያዝ ላይ ለሚገኙ ፣ ዘግይተው ለተዘሩና በተለያዩ የእድገት ደረጃ ላሉ ሰብሎችም ሆነ ቋሚ ተክሎች የውሃ አቅርቦት ከማረጋገጥ አንጻር አውንታዊ ሚና ይኖረዋል ብሏል ኤጀንሲው። እንዲሁም የሚጠበቀው ዝናብ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸውን ለሚያገኙት ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች የማሳ ዝግጅት ለማድረግና ዘር ለመዝራት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ይጠበቃል። ዝናቡ ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎችም በጎ ሚና እንደሚኖረው ያመለከተው የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በተለይ ውሃ አጠር የሆኑ አካባቢዎች የዝናብ ውሃ ለመሰብሰብና ከማከማቸት ወቅቱ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ ይህንኑ ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት እንዲያደርጉ  መክሯል። ከመደበኛ በላይ ዝናብ የሚያገኙና አልፎ አልፎም ከባድ ዝናብ ሊኖራቸው እንደሚችል በትንበያው የተጠቀሱት አካባቢዎች ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደጉም ያሳስባል። ውሃ ማሳ ላይ እንድይተኛ ማድረግ በማድረግ ሰብልን ከአደጋ ለመከላከል ቦይ ማውጣትና ማንጣፈፍ እንደሚገባም መክሯል። እንዲሁም አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ መሰብሰብ እንዳለበት ያሳሰበው ኤጀንሲው የተሰበሰበው ሰብል በእርጥበት ጉዳት እንዳያደርስበት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጿል። በታችኛው ተፋሰሶች ላይ ሊኖር የሚችለው እርጥበት ከላይኛው ተፋሰሶች ጋር ከሚኖረው የወንዝ ፍሰት ጋር ተዳምሮ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል ያለው የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ይህም የወንዝ ሙላትና ቅጽበታዊ ጎረፍ ሊያስከትል ስለሚችል ቅድመ ጥንቃቄና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አሳስቧል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም