የጎንደር ዩንቨርሲቲ ለሁለት ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ

56
ጎንደር ሚያዝያ 27/2010 የጎንደር ዩንቨርሲቲ በመምህርነትና በምርምር የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁለት ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ መስጠቱን አስታወቀ፡፡ ማዕረጉ የተሰጣቸው ምሁራን ከማስተማር ስራ ጎን ለጎን በባዮ ቴክኖሎጂና በሜዲካል ማይክሮ ባዮሎጂ በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎች አከናውነዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ ለኢዜአ እንደተናገሩት የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረጉን ያገኙት ፕሮፌሰር ባዬ ገላውና ፕሮፌሰር ነጋ ብርሃን ናቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሴኔት ህግ መሰረት ተገምግመውና መስፈርቶችን አሟልተው በመገኘታቸው በዩንቨርሲቲው የሴኔት ቦርድ የፕሮፍሰርነት ማዕረጉ በዚህ ሳምንት ጸድቆ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ምሁራኑ ለማዕረጉ የበቁት በማስተማር ብቃታቸው፣ ባበረከቱት የምርምር ስራዎች፤ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በነበራቸው የረዥም ዓመታት አገልግሎትና በማህበረሰቡ ውስጥ ባበረከቱት ማህበራዊ አገልግሎት ነው፡፡ ፕሮፌሰር ባዬ ገላው በሜዲካል ማይክሮ ባዮሎጂ ከ50 በላይ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን በአለም አቀፍና በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ባላቸው ጆርናሎች ለህትመት ያበቁ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ነጋ ብርሃን ደግሞ በባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከ60 በላይ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ያከናወኑና በታዋቂ ጆርናሎችም ስራዎቻቸው ተቀባይነት አግኝቶ ለህትመት በቅቷል፡፡ በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው ፋኩልቲዎች በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች ያገለገሉ መሆናቸውን ዶክተር ደሳለኝ አስታውቀዋል፡፡ የጎንደር ዩንቨርሲቲ የዛሬዎቹን ጨምሮ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሰጣቸው 12 ምሁራን እንዳሉትም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም