በአገሪቷ የታየው ሠላም ዘላቂ እንዲሆን ህዝበ ሙስሊሙ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

68
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 በአገሪቷ አሁን የታየው ሠላም ዘላቂ እንዲሆን ህዝበ ሙስሊሙ የበኩሉን እንዲወጣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ። 1ሺህ 439ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት ተከብሯል። በስነ-ሥርዓቱ ላይ በተመረጡ ዑለማዎች ተክቢራ ተደርጓል፤ የኢድ ሶላትና ኡጥባም ተካሂዷል። የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ አሚን ጀማል ባስተላለፉት መልዕክት፣ የእምነቱ ተከታዮች በጾሙ ወቅት ያሳዩትን መደጋገፍ የዘወትር ተግባራቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል። ''በዓሉ ሲከበር የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ ሊሆን ይገባል'' ያሉት ፕሬዝዳንቱ በተለይ ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎችን በማሰብና በመጠየቅ ማክበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ሼህ መሐመድ አውግዘዋል። ሠላምን የሚያደፈርሱ እንቅስቃሴዎችን ህዝበ ሙስሊሙ በንቃት ሊመክት እንደሚገባ አመልክተው አሁን የታየው አገራዊ ሠላም ዘላቂነት እንዲኖረው ሁሉም የእምነቱ ተከታይ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ በበኩላቸው፣ ''ከተማዋ እኩልነትና ነጻነት የተረጋገጠባት፣ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ተቻችለውና ተከባብረው በሠላምና በነጻነት የሚኖሩባት የዲሞክራሲ ሥርዓት ተምሳሌት እንድትሆን በቁርጠኝነት መረባረብ ይገባል''ብለዋል። የእስልምና እምነት ተከታዮች ህገ መንግስቱ ባረጋገጠው መብት በመጠቀም ሀይማኖታቸውን ከማክበርና ከማስፋፋት ባለፈ በአገሪቷ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል። የሀይማኖት መቻቻል ባህሉ ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መስራት ይገባልም ብለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም