የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዘዳንት ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

93
ጳጉሜ 6/2011  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የ2012 መሻታችን የህዝብ ተጠቃሚነት፤ የጀመርነውን የመጨረስ መሻትና ማዕከላችን ደግሞ የህዝብ ፍለጎትና ተጠቃሚነት ይሆናል አሉ። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። በመልእክታቸውም የ2012 መሻታችን የህዝብ ተጠቃሚነት ነው፣ የጀመርነውን የመጨረስ መሻት ነው፣ ማዕከላችን ደግሞ የህዝብ ፍለጎትና ተጠቃሚነት ይሆናል ብለዋል። ህዝብ በሌለበት ስለ አገር ማውራት ትርጉም የለውም፤ አገር ማለት የተዋቡ ተራራዎችና ሜዳዎች ማለት አይደለም፣ አገር ማለት ህዝብ ማለት ነው የህዝብ አገልጋይ መሆን ደሞ ሀላፊነትን በአግባቡ መወጣት ማለት ነው ብለዋል። በመሆኑም ዛሬ ከጨለማው በስተጀርባ ያለው ብርሃን የምናይበት መንገድ ተከፍቷል፤ ዛሬ እጃችን የገባ እድል ከሰራንበት የትውልድን ታሪክ የምንቀይርበት አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡ አዲሱ ዘመን እንደ ብረት በጠነከረው አንድነታችን የህዝባችንን ሕይወት ለመቀየር ሌት ተቀን ተግተን የህዝባችንን አመክኖአዊ መሻት የምናሟላበት ዘመን መሆኑንም ጠቅሰዋል። 2012 ዓ.ም የህዝብ አንድነት ተጠናክሮ በመደመር ፍልስፍና አገር የምንገነባበት ዘመን መሆኑንም ገልጸዋል። አዲሱ ዓመት በጎ በጎውን አስበንና ሰርተን የህዝባችንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት የምንለውጥበትና ብሩህ ተስፋን የምንሰንቅበት ዘመን እንዲሆን በመመኘት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።   የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል። የኦሮሞ ህዝብ የክረምቱ ዝናብና ጨለማ አልፎ ወደ ጸደይ ብርሃን ሲገባ፣ ጨለማውን አሳልፎ ብርሃኑን ላሳየው ዋቃ ምስጋናን ያቀርባል፡፡ ለሰራው መልካም ሥራዎች ምስጋና ያደርሳል፣ የጎደለውን ለመሙላት ወደ ፊት ያልማል  በማለት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናግረዋል፡፡ የ2012 መሻታችን የህዝብ ተጠቃሚነት ነው፣ የጀመርነውን የመጨረስ መሻት ነው፣ ማዕከላችን ደግሞ የህዝብ ፍለጎትና ተጠቃሚነት ይሆናል፡፡ ለህዝብ ሰርተን ለህዝብ እንኑር፣ ፍትሕን ለህዝብ ሰጥተን በፍትሐዊት እናገልግል፤ ምክንያቱም የኦሮሞ አባባል እንደሚለው ‹‹ጊደር በሌለችበት ኦኮሌን (የወተት መያዣ) ማሰማመር አይጠቅምምና››፡፡ ህዝብ በሌለበት ስለ አገር ማውራት ትርጉም የለውም፡፡ አገር ማለት የተዋቡ ተራራዎችና ሜዳዎች ማለት አይደለም፣ አገር ማለት ህዝብ ማለት ነው የህዝብ አገልጋይ መሆን ደሞ ሀላፊነትን በአግባቡ መወጣት ነዉ፡፡ አዲሱ አመት በጎ በጎውን አስበንና ሰርተን የህዝባችንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት የምንለዉጥበትና ብሩህ ተስፋን የምንሰንቅበት ዘመን ይሁንልን፡፡ አዲሱ ዘመን እንደ ብረት በጠነከረው አንድነታችን የህዝባችንን ሕይወት ለመቀየር ሌት ተቀን ተግተን የህዝባችንን አመክኖአዊ መሻት የምናሟላበት ዘመን ይሁንልን! 2012 ዓ.ም የህዝብ አንድነት ተጠናክሮ በመደመር ፍልስፍና አገር የምንገነባበት ዘመን ነው የኢሬቻ ከ 150 ዓመታት በኋላ መመለስ በዚያን ጊዜ ከነበረው የኦሮሞ አንድነት ጋር ገዳ እንደሚመለስ ያረጋግጥልናል ፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ‹‹መሬት ባለቤት አለው፣ ፍትሕ እውነት አለው፣ ገዳ ህዝብ አለው›› ይላል፣ አንድነት ደግሞ የዛሬ ትውልድ አለው፡፡ በመወያየት፣ በመደማመጥ በመረዳዳት የተጓዝነው ኦሮሞነት፣ ትናንት ጀግኖቻችን የተፋለሙለትን ዓላማ ያረጋገጠ ነው፡፡ ዛሬ ከጨለማው በስተጀርባ ያለው ብርሃን የምናይበት መንገድ ተከፍቷል፤ ዛሬ እጃችን የገባ እድል ከሰራንበት የትውልድን ታሪክ የምንቀይርበት ነው፡፡ በመደመር ፍልስፍና አገር እንገንባ፣ አሁን የደረስንበት የትግል ምእራፍ ትግል ካለፈዉ ይልቕ ቀጣዩ ጉዟችን በሰከነና በሰለጠነ መንገድ በአውቀት፣ ለአገራችንና ህዝባችን የገባነውን ቃል ማሳካትና የጀመርነውን የለውጥ ጉዞ ማስቀጠል ነው፡፡ 2012 ዓ.ም የኦሮሞን ባህልና ማንነት ቀጣይ ትውልድን የምናስተምርበት ዘመን ነዉ ዛሬ የደረስን ቦታ የደረስነው ከመግደል ይልቅ በሐሳብ ሞግቶ ማሸነፍ ፣ አቃፊነትን ከገዳ ሥርዓት ስለተማርን ነው ፡፡ በትናንት ታሪክ ውስጥ እንደ መስታወት ራሳችንን እያየን የምናወድሰው የአሮሞ ትግል፣ ነገሮችን ተመልክተን እንዴት ልንጓዝበት እንደሚገባ የሚያሳየን የድል መላ ስላለው ነው፡፡ የኦሮሞን ባህልና እሴቶች የሕይወት መርሕና የዕለት ሥራችን መመሪያ ካደርግን የሰማዕቶቻችንን አደራ አከበርን ማለት ነው፣ ኦሮሞነትን ለቀጣዩ ትውልድ አወረስን ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በምናከናውናቸው ሥራዎች ሁሉ የኦሮሞን ባህል እሴቶች መርህዎቻችን እናድርጋቸው ፡፡ በ2012 ምን ሰራን ስንል መስፈርቶቻችን የኦሮምን ባህል እሴቶች ምን ያህል ተጠቀምን፣ ምን ያህል ዉጤት አስመዘገብን ፣ ምንስ ያክል የህዝብ እርካታ አረጋገጥን የሚሉት መመዘኛችን ይሆናሉ፡፡ የገዳ ሥርዓታችን፣ ብዝሃነት የማቀፍ ሰንሰለት ነው! የገዳ ሥርዓት ያስተማረን ፍቅርን ነው፡፡ ከኦሮሞነት ጋር መኖር ስንል በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር በጉድፈቻ የሥጋና የደም ዘመድ ማድረግ፣ በሃማቺሳና ሞጋሳ ዘመድ ማፍራት፣ በእልመ በርጩማና በእልመ ምጢ ከሌሎች ጋር በመካፈል መጠቀምና ኦሮሞነት የሚያጎናጽፈውን ሙሉ መብት መጠቀም ራሱን በራሱ የሚገልጽ እውነታ ነው፡፡ ይህ ዛሬም ቢሆን የምንኮራበት ባህላችን ነው፡፡ አሁን ባለንበት ምእራፍም የገዳ ሥርዓት ፍሬ የሆኑ መልካም እሴቶቻችን፣ ከአገራችን ብሔርና ብሔረሰብ ጋር ሆነን ወደፊት በመራመድና አብረን በመስራት የበለጸገች አገር ለመገንባት ታላቅ ጉልበት ሆነውን ያገለግሉናል፡፡ 2012 ዓ.ም ሠላምና የህግ የበላይት ተረጋግጦ፣ ኦሮሞና አሮሙማ ሠላም መሆኑን የምናሳይበት ዘመን ነው!! ኦሮሚያ የባህልና ባህላዊ ትውፊቶች ምድር ናት ስንል፣ ሠላም ከገዳ ሥርዓት ምሰሶዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የራስን፣ የጎረቤትን፣ የዘመድን፣ የአገርንና የሰውን ሠላም መመኘት የኦሮሞነት ምርቃት ነው፡፡ ስሆነም ከዚህ በኋላ ኦሮሚያ ውስጥ ሠላምን ማሰናከል አይደለም ለማሰናከል መሞከር አይቻልም ፡፡ የእኛን ሠላም የህዝብ ሠላም ለማድረግ፣ የደህንነትን መዋቅር ማጠናከርና የህግን የበላይነት ማክበር የሁሉም አካል ድርሻ ይሆናል፡፡ 2012 ዓ.ም ድህነት ተቀርፎ ለምጣኔ ሐብታችን ሌት ተቀን የምንተጋበት ዘመን ነው  ህዝባችን ባለፉት ታሪካችን ውስጥ ለምጣኔ ሐብታዊ ተጠቃሚነት ያደረገው ተጋድሎ ከዘመን ዘመን የሚታወስ ነው፡፡ በአንድ ጎኑ በእኩልነትና በፍትሕ ላይ የተመሠረተ ጥቅምን ማጣቱ፣ በሌላ ጎኑ ደግሞ ተፈጥሮአዊ ሐብቱ ወደ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አለመለወጡ ህዝባችን ዘንድ ሲነሱ የቆየ ቅሬታዎች ነበሩ፡፡ ተፈጥሮአዊ ሐብታችንን ወደ ምጣኔሐብት ቀይረን የኅብረተሳባችንን ችግር ከመሠረቱ ካልፈታን በስተቀር ፖለቲካ ምግብ አይሆንም ፡፡ ይህን የምናደርግበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ቀንና ሌሊት መስራት፣ ለሐብታችን አጠቃቀም ምሪት መስጠት፣ የገቢ ምንጫችንን ማስፋት፣ ገቢን በተገቢ መልኩ መሰብሰብ፣ ከድህነት ወጥተን ወደ ብልጽግና ለመግባት ኢኮኖሚውን መምራት፣ በሁሉም የምጣኔ ሐብት እድሎች መጠቀም በዚህ ወሳኝ ጊዜ የሚጠቅሙንን ጉዳዮች ናቸው፡፡ እርሻን በማዘመን ክረምትና በጋ በማምረት ምርታማነትን ማሳደግ፣ የኢኮኖሚ ግብዓትን በመጨመር ኢንዱስትሪን ማስፋፋት፣ የህዝብ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነትን መሰረት ያደረገ የኢንቨስትመንት አሰራር መዘርጋትና ወደ ሥራ በማስገባት ኦሮሚያን የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ ማዕከል ማድረግ በ2012 ዓ.ም መፈጸም የሚገባቸው ተግባራት ናቸው፡፡ ፋይናንስን በመምራትና ወደ ገበያ ማስገባት፣ አርሶ አደሩ በማደራጀት ከሐብታችን እየተጠቀምን ዘመናዊ ንግድ ውስጥ መግባት፣ አሻጥርና ሌብነትን ከምንጩ ማድረቅ የአዲስ ዘመን ግባችን መሆን አለበት፡፡ 2012 የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄዎች መሠረታዊ መቋጫ የሚያገኙበት ዘመን ነው! አሁን ያለንበት ጉዞ በአንድ ጎኑ በተደራጀ መንገድ በመንቀሳቀስ በኢኮኖሚ መበልፀግን የሚጠይቁ በሌላ መንገድ ደግሞ ሁሉም አካላት ተልዕኮ ተቀብለው በሙሉ ልብ ተልዕኮውን መወጣትና ለጋራ ዓላማ ታዛዥ መሆንን ይጠይቃል፡፡ እኛ የማንጨርሰው አንጀምርም፣ የእውነተኛ መሥዋዕት አሸናፊነት በህግም በታሪክም ይሰራል፣ ያገኘነውን ድል ይበልጥ በማስፋት በ2012 ዓ.ም የኦሮሞ ህዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ የጀመርነውን ጨርሰን ከዳር የምናደርስበት ዘመን ነዉ፡፡ ኦሮሙማ ያስተማረን በጋራ ሆነን ከሰራን በጋራ ከግብ እንደምንደርስ ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም ባህልና ትውፊቱን የሚያውቅ፣ በስነ ምግባር፣ በአዕምሮና በአካል የበሰለ ትዉልድን በመቅረጥ የትዉልድ ቅብብሎሽን የምናሳካበት ዘመን ነዉ! ትምህርት የጉዞአችን ብርታትና የችግራችን ቁልፍ እንዲሁም ዓለምን የምንመለከትበትና በእውቀት ትውልድን የምንገነባበት ማያ መነፅራችን ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ዜጎች የትምህርት እድል እንዲያገኙ ብቻ ሳይሆን ባህልና እሴቶቻቸዉን አውቀው ሌሎችን እንዲያስተምሩ ለማድረግ ፣ ከዓለም ጋር ሰልጥነው በአዲስ ሥልጣኔ ውስጥ የነቃና ተወዳዳሪ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር፣ የትምህርት ልማት ሥር እንዲሰድና የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የነገን ትውልድ የምንገነባበት ዘመን ነዉ፡፡ ጤነኛ፣ በአዕምሮና በአካል የነቃ ትውልድ ለመፍጠር፣ የጤናን አገልግሎት ማስፋፋት፣ ጥራቱን መቆጣጠርና ማስተዳደር ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫችን ይሆናል፡፡ በ2012 ዓ.ም የነገው ትውልድ መልካም እድል በዜግነት አገልግሎት ተሳትፎ ማሳካት የዛሬው ትውልድ እድለኛ ትውልድ ነው፣ ምክንያቱም የጀግኖቻችን አርአያነት መንገዳችንን ያበጅልናል፣ የህዝባችን ታጋሽነት ለምንፈልገው ዓላማ ያደርሰናል፣ የባህላችን ትውፊቶች በውይይት ቅርጽ እያገኙ የጉዞአችንን ድካም ይቀንሱልናል፡፡ ለእኛ ብሎ የደማን ወገን፣ የዛሬዋን ፀዴይ እንድናይ የተሰዋን የምናወድስበት ለእኛ ብሎ የወደቀዉን በጉልበታችን ፣ በእዉቀታችንና በሀብታችን የምናቃናበት ዘመን ነዉ ፡፡ አረንቋ ውስጥ ማቆየት እድለኛነታችንን ማጨለም ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን የምንመኛትንና የበለጸገች ኦሮሚያ ለመፍጠር መመኘት ብቻ ከግብ አያደርሰንም፣ በተስተካከለና ምቹ መንገድ ብቻ ማሳካት አይችልም ፡፡ በየትኛው ሥፍራ ቢሆን በነጻ የሚገኝ ግብር የለም፡፡ የትግል ስኬት የለውጥ ሐሳቦችን ማፍለቅ፤ የዜግነት ግዴታን መወጣት፣ በመወያየትና በማወያየት የጋራ የሆነ ጽንሰ ሐሳብ ማዘጋጀትና የአፈጻጸም ስልት ሆኖ እንዲያገልግል ማድረግን ይጠይቃል፡፡ በሌላ መንገድ፣ ችሎታ፣ ብቃት፣ የተደራጀ ኃይል፣ ጊዜና ያለንን ሐብት ለዜጎቻችን ሕይወት መቀየር ላይ ማዋልን ያፈልጋል፡፡ አሁን ያለንበት ጉዞ በአንድ ጎኑ በተደራጀ መንገድ በመንቀሳቀስ በቂ ጉልበት እያፈሩ መሄድን የሚጠይቅ ሲሆን፣ በሌላ መንገድ ደግሞ ሁሉም አካላት መብትና ግዴታዉን በዉል ተገንዝቦ የተሻለ አገር ለመገንባት የዜግነት ሀላፊነትን በትዉልድ ቅብብሎሸ ሰንሰለት መወጣት ነዉ፡፡ ስለሆነም በመላ ኦሮሚያ ክልል ነባር የኦሮሙማ እሴቶችን የህይወት መርህ በማድረግ ቀንና ሌሊት እየሰራን፣ በሁሉም ረገድ ተወዳዳሪ በመሆን ኦሮሚያንና አገርን በቅንነትና በአንድነት ገንብተን፣ ታሪክን የሚያወራ ሳይሆን ታሪክን የሚሰራ ትውልድ መሆናችንን የምናረጋግጥት ዘመን ነው፡፡ 2012 ዓ.ም የቆሸሸ አስተሳሰብ የሚጸዳበትና፣ በአዲስና በይቻላል መንፈስ ነገን አሻግረን የምንመለከትበት ዘመን ነው የኦሮሞ ህዝብም ሆነ የአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች የአብሮ መኖር፣ የሰላምና በይቅርታ የመሻገር ልማድ አላቸው ፡፡ በአሁን ሰዓት ግን የበሰበሰና ኋላቀር አስተሳሰቦች እና የተግባር መቆሸሽ ህዝብን ከህዝብ ፣ ኃይማኖትን ከኃይማኖት ለማጋጨት የሚኳትኑ ከንቱ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች የሚስተዋሉበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ ፡፡ የዚህ ሐሳብ ዋሻ ከዘመናችን ጋር የማይሄድ፣ የእኔ ይበልጣል ስሜት፣ ከሰው ክቡር ያፈነገጠ የቆሸሸና ያረጀ ያፈጀ አስተሳሰብና ህዝባችን ያየውን ብሩህ ተስፋ ለማጨለም የሚወራጭ ነው ፡፡ ነገር ግን በፍጹም አይሳካለትም፡፡ አዲሱ ዘመን የአገራችን ህዝቦች አንድነታቸውን አጠንክረው፣ አንድነትንና እኩልነትን የሚያጨቀይ ቆሻሻን የሚያጸዱበትና በተስፋና በይቻላል መንፈስ አዲሱን ዓመት የሚቀበለቡት ዘመን ይሆንልናል፡፡ በመጨረሻም፣ 2012 ዓ.ም የብልጽግና፣ በአንድነት በመደመር እሳቤ፣እጅ ለእጅ ተያይዘን በድህነት የምናፍርበት ሳይሆን በላባችን ለፍተን ድህነትን አሳፍረን የፍሰሃ ትውልድ የምናፈራበት ዘመን ይሁንልን! መጪው ዘመን የብርቱ አንድነት ዘመን፣ የብዝሃት ውበት የዳበረበት፣ እውነትና ፍትሕ የሚያሸንፍበት ፣ በሁሉም መስክ የህዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ተረጋግጦ ብሩህ ተስፋ የምንሰንቅበት፣ ለጉዟችን መስመር ስኬት፣ የህዝባችን ህይወት በተሻለ ደረጃ የሚለወጥበትና የደስታና የፍሰሃ ዘመን እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡ ኦሮሚያን እንገነባለን፣ አገር እናቃናለን ፣ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን እናረጋግጣለን!! መልካም አዲስ አመት  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም