ለተማሪዎች የቀረበው የጽህፈት መሳሪያና ደንብ ልብስ ለትምህርት ጥራት አስተዋጽኦ አለው

91

ጳጉሜ 6/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮ ዓመት ለተማሪዎች የጽህፈት መሳሪያና ደንብ ልብስ ማቅረቡ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ አስተዋፅኦ እንዳለው የትምህርት ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

በ2012 የትምህርት ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተተገበሩት መርሃ ግብሮች መካከል በአዲስ አበባ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከተማ አስተዳደሩ በጀት በመመደብ የደንብ ልብስ ለመግዛት መወሰኑ አንዱ ነው።

የደንብ ልብስና የትምህርት ቁሳቁሰ ስርጭት ሂደትና ያለውን ፋይዳ አስመልክቶ ኢዜአ የትምህት ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአቢሲኒያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር አስማማው ሙሉጌታ እንዳሉት የደንብ ልብስ በመንግስት መገዛቱ በተማሪዎች መካከል አንድነትን የሚፈጥር፣ የተቸገሩ ተማሪዎች ሳይሳቀቁ በወቅቱ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመጡና ሙሉ ትኩረታቸውን ለትምህርት እንዲሰጡ በማድረግ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ አስተዋጽኦው የጎላ ነው ይላሉ።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወንድሙ ኡመር በበኩላቸው ትምህርት ቤት በሚከፈትበት ወቅት በርካታ ተማሪዎች የደንብ ልብስ ለሟሟላት ያጠፉ የነበረውን የትምህርት ግዜን  እንደሚያስቀር ነው የተናገሩት።

ክፍለ ከተማው ከ24 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የደንብ ልብስ ከከንቲባ ፅህፈት ቤት እየተረከበ  ነው ያሉት አቶ ወንድሙ፤ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ላሉ ትምህርት ቤቶች በአጭር ጊዜ በማሰራጨት ትምህርት በወቅቱ እንዲጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ወቅት የተማሪው ደንብ ልብስና የትምህርት ቁሳቁስ በመንግስት መሸፈኑ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ ካለው አስተዋፅኦ በላይ ለወላጆችም ኑሮን በመደጎም በኩል ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑንም ነው ሃላፊው የተናገሩት።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት የትምርት ቤት መሻሻልና ሱፐር ቪዥን ቡድን መሪ አቶ ሄኖክ አበበ አብዛኛውን የደንብ ልብስ  መረከባቸውን ተናግረው፤ ተማሪዎች ወጥ በሆነ ሁኔታ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ ለወላጆች  የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት አቅም ያላቸው ተማሪዎች በወቅቱ በተሟላ ሁኔታ ወደ ትምህርት ገበታቸው  የሚመጡ ቢሆንም፤ የደንብ ልብ ወጥ በሆነ መንገድ በመንግስት ወጪ መቅረቡ አቅም የሌላቸው ተማሪዎች ያባክኑ የነበረውን የትምህርት ግዜን ከማስቀረትም በላይ በከተማዋ ባሉ ትምህርት ቤቶች ወጥ የሆነ አለባበስ እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት በበኩላቸው፤ በከተማዋ 183 በቅድመ መደበኛ፣ 64 በ ዜሮ/0/ ክፍል፣ 232 አንደኛ ደረጃ  እና 73 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ወጥ የሆነ የደንብ ልብስ ተዘጋጅቶ ወደ ሁሉም ክፍለ ከተሞች መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡

በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ለትምህርት ቤቶች በማሰራጨትም ከ400 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ መፈጠሩን ነው አቶ አበበ ያስታወቁት፡፡

ወጥ የሆነው ዩኒፎርም በመንግስት ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ መዘጋጀቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ የከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ዘርፍ  ልዩ ትኩረት መስጠቱን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ሀጂ ሸምሱ ናስር በበኩላቸው መንግስት የተማሪዎችን የደንብ ልብስ ና የትምህርት ቁሳቁስ መሸፈኑ፤ በተለይ መስከረም ወር በርካታ ወጪ የሚወጣበት ወቅት በመሆኑ ከፍተኛ እዳ እንዳቃለለላቸው ነው የተናገሩት፡፡

ድጋፉ ለችግረኛ ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆን የወቅቱን የኑሮ ውድነት ያገናዘበ በመሆኑ አስተዳደሩ ምስጋና ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም