በአምቦ ከተማ የበዓል ገበያ የምርቶች ዋጋ ጨምሯል

57
አምቦ  ጳጉሜን 6/2011 በአምቦ ከተማ በዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ በዋለው ገበያ የፍጆታ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ሸማቾች ገለጹ። የከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት በበኩሉ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክቷል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሸማቾች እንዳሉት ከሁለት ወራት ወዲህ በሽንኩርት፣ ዳቦ ዱቄት፣ ስጋ እና ጤፍ ምርቶች ዋጋ ጨምሯል። ከሸማቹች መካከል ወይዘሮ ሙሉ ፊጣ 15 ብር የነበረው ቀይ ሽንኩርት 34ብር እና የነጭ ሽንኩርት ከ80 ወደ 200 ብር በኪሎ እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል። የዳቦ ዱቄት በኪሎ 22 ብር የነበረውን 13 ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ወይዘሮ በቀለች ፈይሳ በበኩላቸው ከሁለት ወራት በፊት 2ሺህ300 ብር የነበረው የአንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ ዋጋ አሁን ላየ 3ሺህ ብር መድረሱን ገልጸዋል። ቅቤ 260 ብር ፣ ኮረሪማ 360 ብር በኪሎ እየተሸጠ ነው። ከአንድ ወር በፊት አንድ ኪሎ ስጋ 180 ብር የነበረው ወደ በ240 ብር ከፍ ማለቱን የተናገሩት ደግሞ አቶ አበበ ፈከንሳ ናቸው ፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ  መንግስት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪውን በመቆጣጠር መፍትሄ እንዲሰጣቸው የሚፈልጉ መሆናቸውን አመልክተዋል። በሸቀታሸቀጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ አቶ አሊ መሃመድ ምርቱ ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚደርጉት ከአከፋፋዮች የዋጋ ጭማሪ ስለሚደረግባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በሽንኩርት ሽያጭ ላይ የተሰማራው በቀለ ፈይሳ ሽንኩርት ከአዲስ አበባ አትክልት ተራ በውድ ዋጋ ስለሚገዙ ጨምረው እንደሚሸጡ ገልጸዋል፡፡ በአምቦ ከተማ አስተዳደር ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት የንግድ ስራ ተቆጣጣሪ አቶ ጉርሜሳ ቤክሲሳ  "ነጋዴዎች በምርታቸው ላይ ያላግባብ  የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ በየጊዜው ግንዛቤ እየሰጠን ነው "ብለዋል፡፡ በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት አማካይነት 1ሺህ 66 ኩንታል ስኳርና 40ሺህ 830 ሊትር የምግብ ዘይት  በማስመጣት ለነዋሪው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያከፋፍሉ መደረጉንም አስረድተዋል። የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል በመከታተል እርምጃ ለመውሰድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም