በአዲስ ዓመት በክልሉ ለሰላምና ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የተለየ ትኩረት ይሰጣል--- አቶ ተመስገን ጥሩነህ

94
ጷጉሜ 5/2011 በአማራ ክልል በአዲሱ ዓመት ሰላምና መረጋጋትን በማጠናከር ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ። ርዕሰ መስተዳደሩ አዲሱ ዓመት አስመልክተው ለጋዜጠኞች እንደገለጹት አዲሱ ዓመት ኃይማኖት፣ ብሄርና ቋንቋ ሳይለይ ሁሉም በአንድነት ሊከብረው የሚገባ ልዩ በዓል ነው። ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልልም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ግጭት፣ መፈናቀልና አለመረጋጋቶች በስፋት የተስተዋሉበት እንደነበር አስታውሰዋል። በተለይም ያለፈው ዓመት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩና ሌሎች አመራሮችም  በሞት የታጣበት ዘመን  በመሆኑ በቀላሉ ሊረሳ የማይችል ወቅት መሆኑን አመልክተዋል። ካለፉት ችግሮች ትምህርት በመውሰድም በመጪው  ዓመት በአዲስ ጉልበት ለሰላምና መረጋጋት የተለየና የተቀናጀ ስራ ለመስራት እቅድ ተነድፎ ተግበራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ርዕሰ መሰተዳደሩ ገልጸዋል። ክልሉ የቀደመ የሰላም ተምሳሌትነቱን በማምጣት ለቱሪዝምና ለሌላውም ልማት እንቅስቃሴዎች እንቅፋት የማይፈጥር የተረጋጋ አካባቢን ለመፍጠር ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ እንደሚሰራ አስታውቀዋል። የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ለፀጥታ መዋቅሩ ብቻ የሚተው ሳይሆን ወጣቱ፣ ምሁራን፣የኃይማኖት አባቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ከመንግስት ጎን በመሆን በባለቤትነት እንዲንቀሳቀሱም አመልክተዋል። ከአጎራባች ክልሎች ጋርም በሰላምና ደህንነት ዙሪያ በጋራ እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳደሩ ጠቅሰዋል። የመገናኛ ብዙሃንም  ከአፍራሽ ተግባራት ተቆጥበው ስለ ሰላምና ልማት ህብረተሰቡን በማንቃትና በማስተባበር የተጠናከረ የገጽታ ግንባታ ስራዎችን  ሊደግፉ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በአዲሱ  ዓመት ከሰላምና ልማት ስራው ባልተናነሰ የወጣቶች የስር እድል ፈጠራን ከልማዳዊ አሰራር በማላቀቅ መሰረታዊ ችግር የመፍታት ስራ እንደሚከናወን አቶ ተመስገን ተናግረዋል። "ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራም ለግብርና እድገቱ እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችን በማሻሻልና በመተግበር በርካታ ወጣቶችን የሚሸከም ማዕቀፍ ሆኖ ይሰራል" ብለዋል። ርዕሰመስተዳድሩ እንዳሉት በኢንቨስትመንት ዘርፉም የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ ለስራ እድል ፈጠራው የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማስቻል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው። በራሱ አቅም እያደገ የመጣውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በተሻለ አሰራር በማገዝ ለስራ እድል ፈጠራው ጠቀሜታ እንዲውል በተለየ ትኩረት እንደሚሰራ  አብራርተዋል። በእነዚህና ሌሎች የልማት አመራጮች በመጠቀምም በ2012 ዓ.ም ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ ወጣቶች  የስራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን አስታውቀዋል። የታቀደው የስራ እድል ፈጠራ ውጤታማ እንዲሆንም ወጣቶች የስር ፍቅርና ፍላጎት ኖሯቸው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አሳስበዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ ለክልሉና ለሌሎችም ኢትዮጵያዊያን አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የልማት የብልጽግና፣ የመተሳሰብ ዓመት እንዲሆን ምኞታቸውን ገልፀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም