በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን የሚልቁ ጨቅላዎች በጤና ተቋማት ይወለዳሉ

56
ጷጉሜ 5/2011 በኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ እናቶች ወልደው ለመሳም፤ ትውልድ ለማስቀጠል ጉዞ ቢጀምሩም በጤና ተቋም የሚወልዱት ግማሽ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። የጤና ሚኒስቴር በመጪው 2012 ዓ.ም የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር 90 በመቶ የማድረስ እቅድ አንግቦ እየሰራ ነው። በአገሪቱ በጤናው ዘርፍ በርካታ ውጤቶች ቢመዘገቡም በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር በሚፈለገው ልክ አድጎ የጨቅላ ህጻናትን ሞት መግታት አላስቻለም። አሁንም 50 በመቶ የሚሆኑት እናቶች ከጤና ተቋማት ውጭ ይወልዳሉ፤ በዚህና በሌሎች ምክንያቶችም በርካታ ህጻናት ሕይወታቸውን በአጭሩ እንደሚያጡ መረጃዎች ያመላክታሉ። ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ በሰለጠነ ባለሙያ የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር ከ28 ወደ 50 በመቶ ማድረስ ቢቻልም ዛሬም በጤና ተቋማት ከሚወለዱ አንድ ሺህ ጨቅላዎች 50 የሚሆኑት ይሞታሉ። ከጤና ተቋማት ውጭ የሚወለዱ ህጻናት የሞት ምጣኔ ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል። ጨቅላ ህጻናት በተወለዱ በ28 ቀናት ለሞት የሚዳረጉበት ምክንያት ከነፍሰጡር እናት ጤንነትና አመጋገብ፣ የእርግዝና ክትትል፣ በወሊድ ወቅትና ከወሊድ በኋላ እንክብካቤ ጋር ይያያዛል። የግንዛቤ ማነስና የጤና ተቋማት አገልግሎት በሚፈለገው ደረጃ ያለመሆን ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና አፍላ ወጣቶች የጤና ቡድን አስተባባሪ አቶ ዘነበ አካለ ይገልጻሉ። ከተደራሽነት ባሻገር የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ በሚፈለገው ደረጃ ባለመሆኑ በርካታ እናቶች በቤታቸው ያለ ጤና ባለሙያ እርዳታ ይወልዳሉ። እንደ አቶ ዘነበ ገለጻ በ2012 ዓ.ም በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር ለማሳደግ ሰፊ ዕቅድ ተነድፏል። በየዓመቱ በጤና ተቋማት ከሚወለዱ ሁለት ሚሊዮን ጨቅላ ህጻናት መካከል ሁሉም በሕይወት እንዲቆዩ ለማድረግ የእናቶችን የጤና አገልግሎት ማሻሻል ዋነኛው ተግባር እንደሆነም ገልጸዋል። ሚኒስቴሩ በ2012 ዓ.ም በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችን አሃዝ 90 በመቶ ለማድረስም ወጥኗል። የጤና ተቋማትን የቅብብሎሽ ስራና የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት የሚጠቀሙ እናቶችን ቁጥር ማሳደግ እንዲሁም የእናቶችን የጤና ተቋማት ቆይታ መጨመር ዋነኛ ተግባራት ናቸው። ክትትል ለማድረግ ወደ ጤና ተቋማት ከሚመጡ 72 በመቶ እናቶች ክትትላቸውን ጨርሰው መውለድ የሚችሉትን ሙሉ በሙሉ ክትትላቸውን እንዲጨርሱና በጤና ተቋም እንዲወልዱ ማድረግ ነው። በተጨማሪም ያለ ዕድሜ ጋብቻን በማስቀረት ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ከፍተኛ እገዛ አለው ብለዋል አስተባባሪው። በቅርቡ የወጣ መለስተኛ የስነ ህዝብና ጤና ዳሰሳ ጥናት ባለፉት ሶሰት ዓመታት ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገቧን አመላክቷል። ያም ሆኖ የጨቅላ ህጻናትን ሞት በመቀነስ የሚፈለገው ውጤት ባለመመዝገቡ በቀጣይ በትኩረት መስራት እንደሚያሻ ጠቁሟል። በመሆኑም በመጀመሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር በሁለተኛነት ደግሞ የጤና ተቋማትን አገልግሎት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል አቶ ዘነበ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም