ለግብር ከፋዩ የሚሰጠው እውቅና ታማኝነትን እንደሚጨምር ግብር ከፋዮች ተናገሩ

78
አዲስ አበባ ኢዜአ ጳጉሜ 5 / 2011 በመንግስት በኩል ለግብር ከፋዩ የሚሰጠው እውቅና በቀጣይ በታማኝነት ግብርን ለመክፈል የሚያነሳሳ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ግብር ከፋዮች ተናገሩ። የአዲስ አበበ ከተማ ገቢዎች ባለሰልጣን በ2011 በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ለ155 ግብር ከፋዮችና ለአሰባሰብ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ለመጀመሪያ ጊዜ የዕውቅና መርሃ ግብር ትላንት አካሂዷል። ለግብር ከፋይዮች የተሰጠው እውቅና የተለያዩ ደረጃዎች ያሉት በመሆኑ 97 ግብር ከፋዮች የብር፤ 41 የሚሆኑ የወርቅና 17 ግብር ከፋዮች የፕላቲኒየም ደረጃ  ተሸላሚ ሆነዋል። በእውቅና አሰጣጥ የተካተቱ ግብር ከፋዮች አምስትና ከዚያ በላይ በግብር ከፋይነት የቆዩና የሂሳብ መዝገብ የሚይዙ ሲሆኑ የህግ ተገዥነትን ጨምሮ 7 መስፈርቶች አሉት። እውቅናው የግብር ከፋይ፣ የዘርፍ፤ የባለድርሻ አካላት፣ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እና የሸማች እውቅና መርሃ ግብሮች ያሉት ነው። እውቅና የተሰጣቸው ግብር ከፋዮች መካከል አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት እውቅናው በቀጣይ ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ ለመክፈል መነሳሳትን የሚፈጥር ነው። ቀደም ሲል ለግብር ከፋዩ ማበረታቻም ሆነ እውቅና ስለማይሰጥ ግብርን መክፈል ግዴታ እንጂ ለአገር ልማት ነው የሚለው እሳቤ ዝቅተኛ እንደነበርም አንስተዋል። በእለቱ ባለፉት 8 አመታት ግብይታቸውን ደረሰኝ እየተቀበሉ በማከናወን ታማኝነታቸውን ካሳዩት ሸማች አቶ ጣሃ ያጀቦ ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል። በሚያከናውኑት ግብይት ለከፈሉት ዋጋ የሚቆረጠውን ተጨማሪ እሴት ታክስ በአገራቸው ልማት ላይ እንዲውል በመረዳት ደረሰኝ የመጠየቅ ባህላቸውን እንዳሳደጉ ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ ባለስልጣኑ በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ ካቀደው 34 ቢሊዮን ብር በላይ ውስጥ 32 ነጥብ 5 ቢሊዮኑን  መሰብሰቡን አንስተዋል። የተሰበሰበው ገቢ ከባለፈው ዓመት የተሻለ ቢሆንም የከተማዋ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ገቢ አንጻር የታክስ ህግን ካለማክበርና በሌሎች ችግሮች የሚፈለገውን ያህል እየተሰበሰበ አይደለም። የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ግብርን በትክክል መሰብሰብ የነጻነትና የዘላቂ ልማት ግቦችን የማሳካት ጉደይ መሆኑን ገልጸዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ግብር ከፋዩና መንግስት በጋራ በሰሩት ተግባር ከተገኙ ስኬቶችና ድክመቶች ትምህርት በመውሰድ በቀጣይ በግብር አሰባሰብ ስርአቱ ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ነው ያነሱት። ከግብር ከፋዩና ከተማ አስተዳደሩ ጋር የተጀመረውን ተግባር በማጠናከር ታማኝነት እንዲያድግ መስራት የቀጣዩ ዓመት ትኩረት ይሆናልም ነው ያሉት። "ከምንገነባው ልማት በላይ ልናስተላልፍ የሚገባው ታማኝነትን ነው" ያሉት ሚኒስትሯ ራሳችንን ከማጭበርበር፣ ከመስረቅና የወረደ ስብዕናን ለልጆቻችን ላለማስተላለፍ ቁርጠኛ መሆን አለብን ብለዋል። ለታማኝነት ዋጋ ሳይሰጡ በአቋራጭ ለመክበር የሚሄዱ የንግዱ ማህበረሰብ ካሉ በማስተማር በጋራ ወደ ህጋዊነት ለማምጣት ይሰራል ብለዋል። አዲሱ 2012 በጀት ዓመት የተገነባች አገር ለትውልድ ለማስረከብ ግብርን በታማኝነት የምንከፍልበት ዘመን እንዲሆን ቃል የምንገባበት መሆን አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም