ፌዴሬሽኑ ለዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር 42 አትሌቶችን ይፋ አደረገ

63
አዲስ አበባ ኢዜአ ጳጉሜ 4 / 2011 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለ17ኛ ጊዜ በዶሃ ለሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶችን ዛሬ ይፋ አደረገ። የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው በኳታር ዶሃ ከመስከረም 17 እስከ 26 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል። በ24 የተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች አትሌቶች የሚፎካከሩም ይሆናል። ኢትዮጵያ በውድድሩ የሚፎካከሩ 42 አትሌቶችን በተለያዩ የውድድር ዘርፎች ለማሳተፍ የመጨረሻ ምርጫ አካሂዳለች። በሁለቱም ጾታ በ10 ሺህ፣ በ5 ሺህ፣ በ1 ሺህ 500፣ በ3 ሺህ  ሜትር መሰናክልና በማራቶን የሚሳተፉ አትሌቶች ተለይተዋል። በወንዶች 5 ሺህ ሜትር ሐጎስ ገብረሕይወት፣ ጥላሁን ሃይሌ፣ ሰሎሞን ባረጋ፣ አባዲ ሐጎስና ሙክታር እዲሪስ ተመርጠዋል። በተመሳሳይ ለተሰንበት ግዳይ፣ ሒዊ ፈይሳ፣ ፋንቱ ወርቁና ፀሀይ ገመቹ  በሴቶች አምስት ሺህ ሜትር ለውድድሩ ተመርጠዋል። ወንዶች በ10 ሺህ ሜትር  ሐጎስ ገብረህይወት፣ ዮሚፍ ቀጀልቻ፣ አንዱአምላክ በልሁ፣ ሰለሞን ባረጋ  የተመረጡ ሲሆኑ በሴቶች አልማዝ አያና፣ ለተሰንበት ግዳይ፣ ነጻነት ጉደታ፣ ሰንበሬ ተፈሪና ፀሀይ ገመቹ በዚሁ ተመሳሳይ ርቀት ይወዳደራሉ። በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች ሳሙኤል ተፈሪና ታደሰ ለሚ የተመረጡ ሲሆን ገንዘቤ ዲባባ፣ ጉዳፍ ፀጋዬ፣ አክሱማዊት አምባዬና ለምለም ሀይሉ በዚሁ ርቀት ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ ይሆናል። በወንዶች በ3 ሺህ ሜትር ጌትነት ዋለ፣ ጫላ ባዩ፣ ለሜቻ ግርማና ታከለ ንጋቱ  በውድድሩ ተካፋይ ናቸው። መቅደስ አበበ፣ ሎሚ ተፈራ፣ ዘርፌ ወንድማገኝና አገሬ በላቸው በሴቶችን 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ይካፈላሉ። በወንዶች ማራቶን ለሊሳ ደሲሳ፣ ሞስነት ገረማው፣ ሙሌ ዋስይሁንና ሹራ ቂጣታ የተመረጡ ሲሆን በተመሳሳይ ሴቶች ደግሞ ሮዛ ደረጀ፣ ሩቲ አጋና ሹራ ደምሴ ይወዳደራሉ። በ800 ሜትር ሩጫ ደርቢ ወልተጂና ጉዳይ ጸጋዬ እንዲሁም 20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር ደግሞ የኋላዬ በለጠው በሴቶች ይሳተፋሉ። ኢትዮጵያ ለንደን ላይ በተካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተካፍላ ሰባተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል። በዚሁ ውድድር 2 ወርቅና 3 ብር በድምሩ 5 ሜዳሊያዎችን ያስመዘገበች ሲሆን አልማዝ አያናና ሙክታር እንድሪስ ወርቅ እንዲሁም ታምራት ቶላ፣ ጥሩነሽ ዲባባና አልማዝ አያና የብር ሜዳሊያ አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም