የዴሞክራሲ ቀን እየተከበረ ነው

63
ጳግሜ 4/2011 የዴሞክራሲ ቀን "በመደመር እሳቤ ጠንካራና ዘላቂ ዴሞክራሲን ለመገንባት እንነሳ" በሚል መሪ ሃሳብ በሸራተን አዲስ ሆቴል በመከበር ላይ ይገኛል። በዴሞክራሲ ቀን አካባበር ላይ የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤዋ ሽታዬ ምናለ የፍትህና የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲጠናከሩ እንዲሁም ገለልተኛ ሆነው አንዲሰሩ መንግስት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል። በተቋማት ውስጥ እየተደረገ ያለውን ማሻሻያና ለውጥ እንደ ምቹ አጋጣሚ በማየት ለዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከርና እድገት በጋራ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል። በዴሞክራሲ ስርዓት ውሰጥ የህዝቡን ተሳትፎ ለማሳደግና ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ህብረተሰቡ ሀሳብን በልዩነት የማስተናገድ ባህል ሊያዳብር እንደሚገባውና ለዚህም መላው ህዝብ ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት የበኩሉን ሃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በዴሞክራሲ ቀን አከባበር ላይ ግጥምና ሙዚቃዊ ድራማዎች እንዲሁም ቀኑን አስመልክቶ የተዘጋጀ አጭር ዘጋቢ ፊልም ለታዳሚያን ቀርቧል። የፓናል ውይይትም የዕለቱ አከባበር አካል እንደሆነ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት "ጳጉሜን በመደመር" በሚል መሪ ሀሳብ የጳጉሜን ስድስት ቀናት የመደመርን ስድስት ምሰሶዎች ባማከለ መልኩ አገራዊ መርሃ ግብር በማካሄድ ላይ ይገኛል። ጳጉሜን 1 የብልፅግና ቀን፣ ጳጉሜን 2 የሠላም ቀን፣ ጳጉሜን 3 ብሔራዊ የኩራት ቀን በሚል የተከበሩ ሲሆን ዛሬ የዴሞክራሲ ቀን በመከበር ላይ ይገኛል። ነገ የፍትህ ቀን በሚል የሚከበር ሲሆን የአዲስ ዓመት ዋዜማ ጳጉሜን 6 ቀን ደግሞ የአገር አንድነት ቀን በሚል ይከበራል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም