የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዋጋ ግሽበት ምክንያት የሆነውን የንግድ መፋለስ ችግርን ይፈታል--ምሁራን

86
ጷጉሜ 3/2011 የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዋጋ ግሽበት  ምክንያት የሆነውን የንግድ ስረአት መፋለስ ለማስተካከል እንደሚረዳ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ገለጹ፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል  ስላለው ድርሻና እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ግሽበት ምክንያት ላይ ኢዜአ  የምጣኔ ሃብት ምሁራንን  አነጋግሯል፡፡ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ  የምጣኔ ሀብት ምሁር  ዶክተር  መኮንን  ከሳሁን በሰጡት አስተያየት  መንግስት እያከናወነ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ለንሮ ውድነት ምክንያት የሆነውን የገበያ ስረአት መፋለስ ለመፍታት እንደሚጠቅም ተናግረዋል፡፡ የኑሮ ውድነቱ በአብዛኛው የሚታየው በሀገር ውስጥ ምርት ላይ በመሆኑ በትክክል  ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ነው ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ መሆኑን  ነው ዶክተር  መኮንን   የተናገሩት ፡፡ በሀገሪቱ ባለፈው አመትም ሆነ ዘንድሮ  የተሻለ ምርት ያለበት መሆኑን  የሚጠቅሱት ባለሞያው በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ የምርትም እጥረት አለ ለማለት የማያስችል በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ምክንያታ አለው ብሎ ለመገለጽ ያስቸግራል ነው ያሉት ፡፡ ለዋጋ ንረቱ ዋናው ምክንያት  የገበያ ስረአቱ መፋለስ በመሆኑ መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚውን ሪፎርም ለማድርግ የጀመረው ስራ ችግሩን ለመቅረፍ የሚጠቅም መሆንን ነው ዶክተር መኮንን የገለጹት፡፡ የገቢያ ስረአቱን ላይ የሚስተዋለውን መፋለስ ማስተካከል ላይ ችግር እንደለው የተናገሩት ባለሞያው በምግብ ሸቀጦች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት  መቆጣጠር እንደሚገባ  ነው የተናገሩት፡፡ በሸማቹና በአምራቹ መካከል ያለው የግብይት ሰንሰለት ረጅም መሆኑ በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ ለዋጋ መናር ሌላው መንስኤ መሆኑንም ነው የጠቀሱት፡፡ በሀገሪቱ እያጋጠመ ያለው የዋጋ ግሽበት ዋነኛ ምክንያት የንግድ ስረአቱ ያልመዘመንና ኋላቀር በመሆኑ ነው ያሉት ደሞ የምጣኔ ሀብት ባለሞያው  አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው ላይ በስፋት የዋጋ ግሽበት ምክንት በግልጽ መለየቱ ጥሩ ነው ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ እየተከሰተ ያለው የዋጋ ግንሽበት  ለመፍታት የውጨ  ባለሀብቱ ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በመቀናጀትም  ቢሆን እንዲገቡ ነጻ ቢደረግ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ነው ባለሞያው የጠቀሱት፡፡ በበርካታ ሀገራት እንደሚታየው በሀገሪቱ ውስጥ ጠንካራ የሸማች ማህበር  በመመስረት የሸማቹን የመደራደር አቅም እንዲኖረው ማድረግና የገበያ ትስስሮችን ማበራከት የዋጋ ንረቱን ለመከላከል መፍትሄ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር መኮንን ናቸው፡፡ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ከአምራች ህብረት ስራ ማህበራት ጋር በቀጥታ በማስተሳሰርና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር የዋጋ  ንረትን  መቀነስ  እንደሚቻል  የጠቆሙት  ዶክተር መኮንን ኢኮኖሚያዊ ምክንያት  የሌለው  ዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም ነው የጠቀሱት፡፡ ከዚህ ባለፈው መንግስት በአንዳንድ እጥረት ባለባቸው ቦታዎች ላይ  ድጎማ የማድርግና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራትን ማጠናከር ይገባዋል ብለዋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው ባለፉት አመታት ስኬቶች የተመዘገበ ቢሆንም የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት በማጋጠሙ ላለፉት በርካታ አመታት እስከ 15 በመቶ የሆነ የዋጋ ግሽበት ማጋጠሙን ነው የገለጹት፡፡ በመሆኑም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን የዋጋ ግሽበትን መንስኤ በመለየት ችግሩን ከመቅረፍ አንጻር  ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸውል፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው  ላይ የተቀመጠው እቅድ የዋጋ ግሽበቱን በተረጋጋ መልኩ በነጠላ አሀዝ እንዲቀጥል የሚረዳ ነው ብለዋል ዶክተር ተካልኝ፡፡ ዶክተር ተካልኝ እንዳሉት ˝ችግሮቹን ለመፍታት  ችግሩን ለይቶ እንዴት ልፈታው የሚለውን ይዞ መነሳት አስፈላጊ ነው˝ ያሉት  ሚኒስትር ዴኤታው በመቀጠልም ለዛ የሚሆን ሰፊ ማሻሻያዎችን መስራት ነው ብለዋል ፡፡ ችግሮቹ ተለይተዋል  የህግ ስራአቱ ተዘርግቱ  መንግስት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ እድገት የሚፈልጉ ሁሉም አካላት ያገባኛል ብለው መስራት እንደሚያስፈልግ ነው የጠቀሱት ፡፡ መንግስት ማክሮ ኢኮኖሚው የገጠመውን ችግር በመፍታት  ግብርናውን የሚያሳድጉ  ተግባራትን በማከናወንና ለቱሪዝምን  ዘርፉ ትኩረት በመስጠት ችግሩን የሚቅረፍ በርካታ አቅም መኖሩኑም ነው የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም