ታሪካዊና ባህላዊ ኃብቶች አገራዊ ኩራትን በመፍጠር አገርን ለመገንባት የሚያግዝ አቅም ይሆናሉ - የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

107
ጳጉሜ 3/2011  በኢትዮጵያ ያሉ ታሪካዊና ባህላዊ ኃብቶች አገራዊ ኩራትን በመፍጠር የተሻለች አገርን ለመገንባት የሚያግዙ እሴቶች በመሆናቸው ዜጎች የአቅም ምንጭ አድርገው ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለፁ። መላው ኢትዮጵያዊያን ሊኮሩባቸውና የሞራል መንፈስ አድርገው ሊጠቀሙባቸው የሚችሏቸው ባህላዊ፣ ታሪካዊና ምጣኔያዊ እሴቶች አሏቸው። በዜጎች ዘንድ የብሄራዊ ኩራት እንዲመጣ፣ በዚህም በአገሪቱ የሚካሄዱት የሰላምና የልማት ውጥኖች እንዲሳኩ የሚያግዝ ሞራላዊ አቅም ለመፍጠር በመላው ኢትዮጵያ ዛሬ ብሄራዊ የኩራት ቀን ተከብሯል። በተለይም በአዲስ አበባ “አዲስ አበባ ቤቴ፤ኢትዮጵያዊነት ኩራቴ" በሚል መሪ ቃል ነው በመስቀል አደባባይ በተሰናዳ ደማቅ ስነ-ስርዓት ብሄራዊ የኩራት ቀን የተከበረው። ቀኑን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በመተሳሳብ ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ጠንካራ ብሔራዊ ኩራትን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል። ታሪካዊና ባህላዊ ኃብቶች አገራዊ ኩራትን በመፍጠር የተሻለች አገርን ለመገንባት የሚያግዙ አቅም ናቸው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ዜጎች እነዚህን እሴቶች የሞራላቸው ምንጭ አድርገው ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባ ተናግረዋል። በእለቱ ብሄራዊ እሴቶች ጉልተው እንዲወጡ በማድረግ የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት ይቻል ዘንድ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል። ለዚህ ደግሞ መካፋፋልን በማስቀረት አንድነትን ማጠናከር የግድ ይላል ሲሉም አመልክተዋል። ዛሬ በአዲስ አበባ በተከበረው የኩራት ቀን ላይ ከ250 ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የታደሙ ሲሆን የከተማው ነዋሪዎችም የተለያዩ የአገር ታሪክንና ባህልን የሚያንፀባርቁ ትርኢቶችን በሰልፍ አሳይተዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም