አንድ ቀን እንደሆነ ያው 24 ሰዓት ነው

172
ያንተስራ ወጋየሁ ከዲላ /ኢዜአ/ ቀናቶችን በወራት ተተክተው ፣ ወራቶች ተቆጥረው ዓመት ሲወልዱ አዲስ ብለን የያዝነውን ዓመት ይጠናቀቅና ሌላ አዲስ ዓመት መቀበል የሁሉ ጊዜ ግዴታችን ነው ። አሁንም አዲስ ዓመት በምንቀበልበት ዋዜማ ላይ እንገኛለን ። እስከ አሁን ድረስ ስንት አሮጌዎችን ሸኝተን ስንት አዳዲስ ዓመታትን ተቀብለን ይሆን? ዳሩ አሮጌውን እየለቀቅን አዲሱ መቀበላችን በራሱ ልዩ ስሜት ቢያጎናጽፈንም በውሎአችን ፣በስራችንና በኑሯችን አዲስ አመትን ልዩ የሚያደርገውን ነገር መለየት አስፈላጊ ነው። ሀገራችንን ከተቀረው አለም ልዩ ከሚያደርጓት በርካታ መገለጫዎች መካከል አንዱ የራሷ የሆነ የዘመን መቁጠሪያ ያለት የ13 ወራት ባለቤት መሆኗ ነው ። በተለይ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በሕዝቦቿ ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር ልዩ ስሜት ይፈጥራል!። እንኳን አደረሰህ/ሽ! ዘመኑ የሠላም፣ የፍቅር ፣ የብልጽግና የደስታ “ይሁንልህ/ሽ“ መባባሉ የአዲስ ዓመት ገፀ በረከቶች ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው ። እውነትም ገፀ በረከት ብንለው ይገልፀዋል ። ከሰላም ፣ ከፍቅር ፣ ከብልፅግናና ከደስታ የበለጠ የለምና ። ታዲያ! አዲሱን ዓመት ተቀብለን የፍቅር እንዲሆን የተመኘነውን ያክል በተቃራኒው የጠብና የጥላቻ ዘመን ሆኖብን ቀናት አልገፋ ብሎን በርካታ አመታትን የረገምን ስንቶቻቸን እንደሆንን ቤት ይቁጠረው ። ዘመኑ የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተን ስናበቃ ያለ አንዳች የኑሮ ለውጥ ጊዜአችንን የገፋን በአንፃሩ ደግሞ ሰርተው የተለወጡ ሌሎች ሰዎችን ዝና ስናወራ ቀናት በላያችን ላይ እየነጎዱ ያመለጡንስ ስንቶቻችን ነን ? አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በአጉል ተስፋ ከመዳከር ይልቅ ቀን እዲወጣልን አቅደን ለተግባራዊነቱ መዳከር ብልህነት ነው። የተድላ የብልጽግና የፍቅር …........ ብለን የተመኘናቸው የተስፋ ቀናት አዲስ ዓመት በመምጣቱ ብቻ ቁጭ ብለን የምናገኛቸው አይደሉም ። ዝግጁነት ፣ የሚተገበር እቅድንና ለመተግበር የሚያስችል ቁርጠኝነትን ይጠይቃሉ ። አለበለዚያ ቀን እንደሆነ ያው 24 ሰዓታት ነው ። ዓመት ካልንም ያው ዻጉሜን ጨምሮ 13 ወራትን የያዘ ነው። አዲስ አመትና እቅድ የአንድ ሳንትም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን የፕላንና ልማት ኮሚሽን በእቅድ አምዱ መግቢያ ላይ አስፍሮታል ፡፡ ይሁንና ከግለሰብ አንስቶ ሀገራዊ እቅዶች በሁለት መሰረታዊ ችግሮች ከግብ ሳይደርሱ በወረቀት ላይ ብቻ እንደሚቀሩ አመላክታል። የመጀመሪያው እቅዱን ለማሳካት የሚረዱ ምቹ ሁኔታዎችን የመለየት ውስንነት ሲሆን ይህም የራስ አቅምንና ከእቅዱ መጠን ጋር ያለማጣጣም ችግር ነው። አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀ ግለሰብ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመግባት ሲያቅድ በአካባቢው ምን ያክል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዳሉ መለየት የመጀመሪያ ስራው መሆን አለበት ። ከዝንባሌውና ከኢኮኖሚ ዝግጅት አንጻር የትምህርት ክፍሉን በጥንቃቄ መለየት አለበት ። ይሁንና በእቅዱ መሰረት በሁለት የተለያዩ ተቋማት ሁለት የተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ለመማር ቢያቅድ የጊዜና የገንዘብ እጥረት ሊያጋጥመው ስለሚችል የመሳካቱን ጉዳይ ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል ። ሁለተኛው እቅድን እንዳይሳካ ተግዳሮት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን መለየት ተገቢ መሆኑን ነው። በትግበራ ሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ቀድሞ የእቅዱን አካል ማድረግ ከተቻለ በቀላሉ ማለፍ ይቻላል ። ሳያቅዱ ውጤታማ ከመሆን አቅዶ ውጤት አልባ መሆን ይሻላል የሚሉት የአካባቢ ጥበቃ ተመራማሪ ዶክተር ታደሰ ክፔ ናቸው ። በድንገት የመጣ ውጤት በድንገት የመጥፋት እድሉ ሰፊ ነውና ይላሉ ። ይሁንና በመጠኑም ቢሆን የተገኘ ትንሽ ውጤት መድረሻ ያለውና የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ዓላማ ያደረገ በመሆኑ ለቀጣይ ስኬት መደርደሪያ ይሆናል የሚል ሃሳብ አላቸው ። በታዳጊ ሀገራት በርካቶች አያቅዱም ። ያቀዱትንም ቢሆኑ የተደራጀ የማስፈጸሚያ ስልት የላቸውም የሚሉት ተመራማሪው አዲስ አመት ሲመጣ ቢያንስ ጥቅል እቅዶችን ማውጣት ለመኖር ተስፋ ይሰጣል ይላሉ ። በተለይ ሀገራዊ እቅዶች ከመንግስት ወደ ህዝብ ብቻ መውረድ የለባቸውም ። ከህዝብም ወደ መንግስት መሄድ መቻል አለበት ። እያንዳዱ ግለሰብ ቢያንስ ሊያበረክት የሚችለውን ድርሻ ማወቅ አለበት ። የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ በበኩላቸው እቅድ መሆን ያለበት በበጀት መጠን ሳይሆን በመስራት አቅም ልክ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በርግጥ እቅዱን ለማሳካት ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ቢሆንም ባዶ እጄ ነኝ ብሎ ከማቀድ መታቀብ ግን ተገቢ አይደለም፡፡ ታዲያ! እቅዳችን የሥራ ፣ የትምህርት ፣ የትዳር ፣ የመውለድ ፣ ሀገር የመቀየር ሌላም ሌላም ሊሆን ይችላል ። ምኞታችንም የማደግ የመለወጥ የመበልጸግ ሊሆን ይችላል ። እቅድን በማሳካት ካሰብነው ግብ ለመድረስ ግን በቅድሚያ የአካልና የስነ ልቦና ዝግጅት ይጠይቃል፡፡ በደንብ በማሰብ የሚተገበር እቅድ ማዘጋጀት ቀጣዩ ምዕራፍ ሲሆን ይህንንም ለቅርብ ሰዎቻችን ብናሳይ የበለጠ ተጠቃሚ እንሆናለን ። በመጨረሻምለእቅዱ መሳካት ቁርጠኛ መሆን ከእኛ ይጠበቃል ማለት ነው ። ይህንን ሁሉ ለፍተን ስናበቃ የተሻለ ቦታና ደረጃ ላይ ባንገኝ እንኳን የበኩላችንን ተወጥተናልና ለሌላ የምናካፍለው ልምድ ይኖረናል፡፡ ከሁሉ በላይ ከዋዛ ፈዛዛ ነጻ በመሆናችን አሉባሌ ቦታ ጊዜውን ከሚያባክንና በበሬ ወለደ ወሬ ሀገርን ከሚያምስ ሰው ጋር ሰነፃፀር እራሳችንን የተሻለ ቦታ ላይ እናገኘዋለን ። የለውጥ ሰው ይበለን ። መልካም አዲስ ዓመት! ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም