የምድረ ቀደምቷ ስጦታ 

55
ሰለሞን ተሰራ (ኢዜአ) በአፍሪካ በህዝብ ብዛቷ ሁለተኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የቸረቻትን ሐብት ወደ ህዝቦቿ ጉሮሮ ለማድረስ ደፋ ቀና እያለች ትገኛለች። አገሪቱ እዚህም እዚያም ፈተና ቢደቀንባትም በህዝቦቿ ትጋትና የአብሮነት ሰንሰለት በመታገዝ ኢንቨስትመንቷን በሌሎች ወዳጆች ለመደገፍ እየታተረች ነው። አገሪቱ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች የአለም አቀፍ ተዋናዮችን ቀልብ በእጅጉ ገዝታለች። ባለፉት አስርት ዘርፈ ብዙ አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ እየተስፋፋ የመጣው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ኢንቨስትመንቱን በመሳብ ግንባር ቀደም ሆኗል። ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው አመታዊ የ 9 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ከአለም አገሮች በግንባር ቀደምትነት እንዳስቀመጣት የአለም ባንክን ጨምሮ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በተመለከተ ጥናት የሚያደርጉ ስመ ጥር ተቋማት በተደጋጋሚ መስክረውታል። “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት 25 አመታት በ10 እጥፍ አድጓል፤ ድህነት ከግማሽ በላይ ቀንሷል፤ የትምህርት ተደራሽነት ደግሞ ከሚገባው በላይ ጨምሯል” በማለት ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ በጥር 2011 ስዊዘርላንድ ዳቮስ ላይ መናገራቸው ይታወሳል። መንግስት ሐብቱን በመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ በማዋል አገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓል። በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ ኢኮኖሚውን ነጻ ለማድረግ በማሰብ በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩትን ኢትዮ ቴሌኮም፣ አቪየሽንና የሃይል ዘርፉን ለግል ባለሃብቱ ለማዛወር ጉዞ ጀምሯል። ኢትዮጵያ ትኩሳት በማያጣው የአፍሪካ ቀንድ መሃል ቆማ ላለፉት ሁለት አስርት በሰላም እየተጓዘች ነው። ከኤርትራ ጋር የነበራትንም አለመግባባት በሰላም በመፍታት ለብዙ አገሮች ምሳሌ መሆን ችላለች። የኢኮኖሚ ጉዞውን መሰረት በማድረግ እ.አ.አ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ጠንክራ እየሰራችም ትገኛለች። ለዚህ ይረዳት ዘንድ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችንና የኢንዱሰትሪ ፓርኮችን በመገንባት ላይ ትገኛለች። አገሪቱ ስኬት ለማስመዝገብ የበቃችው እጇ ላይ ያለውን መሰናክል ለይታ በመጓዟ ነው። ለኢንቨስትመንቱ ፈተና የሆኑትን ከፍ ያለ የስራ አጥነትና የፋይናንስ እጥረት መሰረት በማድረግ ማስተካከያዎች ተወስደዋል። መንግስት ይህንን ችግር ለመፍታት የወሰዳቸው የፖሊሲ ማሻሻያዎችና ስትራቴጂዎች ውጤት በማስገኘት ላይ ናቸው። በዚህም ብዙ ጉልበት የሚፈልጉ ዘርፎችን በመለየት ስራ ፈላጊውን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ግብርናና የግብርና ማቀነባበሪያዎች በኢንቨስትመንት ዘርፉ ቅድሚያ የተሰጣቸው ናቸው። እነዚህ ዘርፎች ጉልበትና ካፒታል የሚፈልጉ ሲሆን አገሪቱ የተትረፈረፈ ጉልበት ቢኖራትም የካፒታል እጥረቱ ግን የማያወላዳ ነው። አገሪቱ በቆዳና ሌጦ ምርት ከአፍሪካ ቀዳሚ ከአለም ደግሞ አስረኛ ደረጃ ላይ ብትቀመጥም በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል ሆኖባት አይን አይኑን ከማየት ውጭ በአግባቡ አልተጠቀመችበትም። ነገር ግን ይህ ሐብት ወደ ገንዘብ ሲቀየር አለም አቀፍ መለያ የያዙ ምርቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ ያደርጋታል። በኢትዮጵያ ያሉ ዋነኛ የኢንቨስትመንት አማራጮች አስተማማኝ የሃይል አቅርቦት ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ካገዟት ሐብቶቿ ቀዳሚው ለሃይል ፍጆታ የምትጠይቀው ዝቅተኛ ክፍያ ነው። በአለም ዝቅተኛ የተባለው ክፍያ ባለሐብቶች የማምረቻ ዋጋቸውን ዝቅ በማድረግ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። አገሪቱ 45 ሺህ ሜጋ ዋት ሃይል ከውሃ፣ 10 ሺ ሜጋ ዋት ከእንፋሎት፣ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት ከንፋስ የማምረት አቅም ቢኖራትም አሁን ላይ ጥቅም ላይ የዋለው 4 ሺ 500 ሜጋ ዋት ሃይል ብቻ ነው ። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የሚያመነጨው 6 ሺ 450 ሜጋዋት አሁን ያለውን የሃይል አቅርቦት ወደ 10 ሺ 500 ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም አሁን ያለውን ክፍያ የበለጠ ዝቅ በማድረግ የአገሪቱን ብልጽግና በአስተማማኝ የሃይል አቅርቦት በመደገፍ በተስተካካለ አቅጣጫ ለመምራት ያስችላል ተብሎ ይገመታል። ዘርፈ ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በአገሪቱ ያለው ዘርፈ ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ የአገሪቱን አጠቃላይ የኢንቨስትመንት መልክ ቀይሮታል። መንግስት እየተከተለ ያለው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ሞዴል ደረጃውን የጠበቀ የቆዳና የቆዳ ውጤቶችና የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን በአጋርነት ለመገንባት የሚያስችል ነው። እ.አ.አ በ2016 በ300 ሚሊዮን ዶላር ተገንብቶ የተመረቀው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አገሪቱን በኢንዱሰትሪ ፓርክ ግንባታ ወደፊት ያራመደና መለያዋ ለመሆን የበቃ ነው። መቀሌ፣ ኮምቦልቻና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም ወደ ስራ ገብተዋል። ኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ኢኮኖሚዋን ከግብርና ጥገኝነት በማላቀቅ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የጀመረችው ጉዞ ጸጋዋን በአግባቡ ለመጠቀም ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል። ባለፈው አመት ወደ አገሪቱ ፈሰስ የተደረገው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ወደ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በማሻቀብ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም አድርጓታል። በአገሪቱ የሚገኙትን ስራ ፈላጊ ወጣቶች ህልም እውን ለማድረግ ታስበው የተገነቡት የሐዋሳ፣ ኮምቦልቻ፣ መቀሌ፣ አዳማና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮች 70 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል አስገኝተዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በ2011 ዓ.ም 103 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘታቸውም የአገሪቱን ለውጥ አመላካች ነው። እ.አ.አ በ2025 የአፍሪካ የማምረቻ ዘረፍ መናኸሪያ ለመሆን አልማ የምትንቀሳቀሰው ኢትዮጵያ ንግድን የሚያቀላጥፉ ምቹ ከባቢ ሁኔታዎቸን ለመፍጠር በእጅጉ እየተጋች ትገኛለች። ለወደብ ያላት ቀረቤታ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የተገነባው የባቡር መስመር 756 ኪሎሜትር ርዝማኔ ያለውና ወደ አገሪቱ የሚገቡና የሚወጡ ሸቀጦችን ለማጓጓዝ ይወሰድ የነበረውን የቀናት ጊዜ ወደ አስር ሰዓት ዝቅ ያደረገ ነው። አገሪቱን በተለያየ አቅጣጫ የሚያገናኙ ተጨማሪ የባቡር መስመሮችም በግንባታ ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያሰፈነችው ሰላምና የመሰረተችው የዲፕሎማሲ ግንኙነት የአሰብንና የምጽዋን ወደብ ለመጠቀም ያስችላታል። ሁለቱ ወደቦች በተለይ ለመቀሌና ለኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያላቸው ቀረቤታ ለኢንቨስትሮች ተጨማሪ ማበረታቻ ተደርጎ ሊቆጠር የሚችልና ያልተነካውን የአገሪቱን የኢንቨሰትመንት አማራጭ እንዲመለከቱ የሚያስችል ነው። ስልጡን አምራች የሰው ሃይል ለማንኛውም ስራ እጅግ አስፈላጊ ነው። ስኬታማ ኢንቨስትመንት ደግሞ በብቁ ባለሙያ መደገፍ አለበት። ይህ ብቃት ሊገኝ የሚችለው በትምህርትና በስልጠና ነው። ኢትዮጵያ የሰለጠነና በስነ ምግባር የታነፀ ሰራተኛ ሐይል በማፍራት በኩል የታደለች ነች ማለት ይቻላል። በአገሪቱ የሚገኙት ከ50 በላይ የመንግስትና የግል ዩኒቨርሲቲዎችና 1 ሺህ 300 የሚጠጉት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችን በማስተማርና በማሰልጠን ወደ ስራ አለም እንዲቀላቀሉ ያደርጋሉ። እነዚህ ስልጡን አምራቾች ደግሞ በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን ኢንቨሰትመንት ወደፊት ለማራመድ የማይተካ ሚና የሚጫወቱና ለኢንቨስተሮች የጀርባ አጥንት መሆን የሚችሉ ናቸው። ለኢንቨስተሮችና አልሚዎች የሚደረግ የታክስ እፎይታ ኢትዮጵያ በምትሰጣቸው የተለያዩ የታክስ እፎይታዎች የኢንዱስትሪ ፓርክ አልሚዎችና ኢንቨስተሮች ተጠቃሚዎች ናቸው። እፎይታው እስከ 10 አመት ሊዘልቅ የሚችል ሲሆን የግንባታ መሳሪያዎችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትና በተመጣጣኝ የሊዝ ዋጋ መሬት ከ 60 እስከ 80 አመት እንዲጠቀሙም ፈቅዳለች። ኢንቨስተሮች እንዳይጉላሉ በማሰብ የተከፈተው የአንድ መስኮት አገልግሎት ከፍተኛ እገዛ አበርክቷል። የተሟላ የመሰረተ ልማትና የሃይል  አቅርቦቱ ኢንቨስተሮቹን ለመሳብ አግዟል። በቅርቡ ለኢንቨስተሮች ውጤታማ፣ አስተማማኝና ወቅታዊ መረጃ እንዲሰጥ ታልሞ የተዘጋጀው የኦን ላይን አገልግሎት ፈቃድ ለማውጣት፣ ለማሳደስና ሌሎች ፍላጎቶችን ለመሙላት ያስችላሉ። በአዲሱ የለውጥ አጀንዳ በመታገዝ እየተደረገ ያለው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የህግና የተቋማት ማሻሻያ በአገሪቱ የንግድ ስራ ለማከናወን የነበረውን ውጣ ውረድ በማስቀረት መንገዱን ቀናና ቀልጣፋ አድርጎታል። በዚህም አገሪቱ ካልተነካው ሐብቷ ኢንቨስተሮች እንዲቋደሱ ጥሪ እያደረገች ትገኛለች። ውብ የመልክዐ ምድር አቀማመጥ፣ አስደናቂ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሐብቶቿ ወደ ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ በመምጣት መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ተጨማሪ የመንፈስ እርካታ የሚሰጡ ናቸው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም