ሕዝቡ የጥፋት ሃይሎችን እኩይ ተግባር ማምከን ይጠበቅበታል - የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

68
አዲስ አበባ ሰኔ 7/2010 በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ጉዞን ለማስቀጠል እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነቱን እንዲወጣና የጥፋት ኃይሎችን እኩይ ተግባር እንዲያመክን መንግስት ጥሪ አቀረበ። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት "የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ እና አገራዊ ድባብ ጠብቆ ማስቀጠል የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆን አለበት" በሚል ርዕስ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እየታየ ነው። በአሁኑ ወቅት እየተፈጠረ ያለው አገራዊ መግባባትና የህዝቦች አንድነት የኢትዮጵያን ተሰሚነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረኮች ውጤት በማስገኘት ላይ መሆኑን አብራርቷል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ እና የአካባቢው ወቅታዊ ሁኔታ ከመሰረቱ የሚለውጥ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኗን ያመለከተው መግለጫው፤ አገራዊ ጥቅሞችን ከማስጠበቅ አልፎ ቀጠናዊ ትስስር በመፍጠር ረገድ ያጋጠሙ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ሌት ተቀን በመስራት ላይ መሆኑን ጠቅሷል። ይህም ቢሆን በአንዳንድ የአገሪቷ ክፍሎች አከባቢያዊ ወሰንና ሌሎች መሰል ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ ለዘመናት አብሮ በኖሩ ህዝቦች መካከል ጥርጣሬን የሚፈጥሩና ለግጭት የሚያነሳሱ ሴራዎች መስተዋላቸውን የጠቆመው መግለጫው፤ "የተፈጠረው ግጭት ህብረተሰቡን የማይወክልና የተጀመረው የለውጥ ሂደት ባልተዋጠላቸው አካላት ጠንሳሽነት እየተመራ እንደሆነ ከወዲሁ መገንዘብ ይቻላል" ሲል ገልጾታል። በመንግስት የለውጥ መሪነት ከቀውስ ለመውጣት የተጀመረው ጥረት እየሰመረ መምጣቱ ያልተዋጠላቸው ሃይሎች እኩይ ድርጊት መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፤ በድርጊቱ የተሳተፉትን አካላት መርምሮ አስተማሪ እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጧል። "የኢትዮጵያ ሕዝብ አምርሮ ሊታገለው የሚገባ አደገኛ አዝማሚያና ተግባር ነው" በማለት መግለጫው አመልክቶ፤ ኢትዮጵያዊያን ይህን ተገንዝበው በጽናት በመታገል የአገሪቷን ሰላም እንዲጠብቁ አሳስቧል። "የህዝቦች ፍላጎት ምንጊዜም ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና እንጂ ብጥብጥና ውድመት አይደለም" ያለው መግለጫው፤ ነፍጥ አንስቶ ሲፋለሙ የነበሩ ወገኖች ሳይቀር የሰላም ጥሪ ተቀብለው በአገር ግንባታ መሰለፍ በጀመሩበት ወቅት የግል ጥቅምን ታሳቢ አድርገው ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚያደርጉት ሩጫ መግታት ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደሚጠበቅ አጽንኦት ሰጦታል። ህዝቡ ለዘመናት ሲንከባከባቸው የኖሩትን የሰላም የአብሮነት የመከባበርና የመረዳዳት የኢትዮጵያዊነት እሴቶች በጥቂቶች ሴራ እንዳይሸረሸር ነቅቶ እንዲጠብቅና እንዲያመክን መንግስት ጥሪውን አቅርቧል። መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች በደረሰ ግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል፤ ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም