ሠላምን መሰረት አድርገው የሚሰሩ ጠንካራ ተቋማት ሊኖሩ ይገባል - ምሁራን

106
አዲስ አበባ  ኢዜአ ጳጉሜ 2/2011ኢትዮጵያ ሠላምን መሰረት በማድረግ ስትራቴጂ ቀርፀው የሚሰሩ ጠንካራ ተቋማት ሊኖሯት እንደሚገባ ተጠቆመ። ታዋቂው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በአንድ ወቅት "እየሳቅንና እየጨፈርን የናድነውን አገር እያለቀስን አንገነባውም" የሚል ጠንካራ መልዕክት ያዘለ ሀሳብ በጽሁፍ ማጋራታቸው ይታወሳል። የታሪክ ተመራማሪው ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ሲናገር "አገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ በቅጡ የተረዳ እንቅልፍ አይተኛም" ማለቱም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የሠላም መናጋት የህልውና ፈተና ከመሆን ባሻገር የአንድን አገር ኢኮኖሚም ያቀነጭራል። ለዚህ ከኮንጎ በላይ ማሳያ የለም፤ አገሪቷ ከራሷ አልፎ ለዓለም የሚተርፍ የውሃ፣ የደንና የከበረ ማዕድን ሀብት ቢኖራትም ሠላም በመጥፋቱ ሐብቷን በአግባቡ መጠቀምና ኢኮኖሚዋን ማሳደግ አልቻለችም። በኢትዮጵያም የሠላም እጦት ስጋት ከሆነ የሰነባበተ በመሆኑ አሁን በአገሪቷ ሠላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ምን ይደረግ? የሚለው ሊመለስ የሚገባው ቁልፍ ጥያቄ ነው። በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የፖሊሲ ጉዳዮች መሪ ተመራማሪ ዶክተር ግርማ ተሾመ በአገሪቷ የቋንቋ፣ የኃይማኖት፣ የብሄር ብዝሃነትና ልዩነቶች ቢኖሩም አያያዙ ተገቢ ባለመሆኑ ለግጭት መንስኤ ሲሆን ይስተዋላል ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል። "ልዩነት የትም አገር አለ" ያሉት ዶክተሩ ይህ ልዩነት የግድ ወደ ግጭት ይወስደናል ማለት አይደለም፤ በሰለጠነ መንገድ በመነጋገር መግባባት በሚቻለው ላይ በመግባባት፣ በማይቻለው ላይ በልዩነት ሠላም ሳይደፈርስ ማስተካከል እንደሚቻል ይገልጻሉ። የአስተዳደር በደል፣ የፖለቲከኞች አድሎአዊ አሰራር፣ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦችና የአመራሩ ቀናኢነት መጓደል ለሠላም እጦት እንደ ምክንያት ሊጠቀሱ ይችላሉ። እንደ ዶክተር ግርማ ገለጻ በአገሪቷ ታሪክ ስምምነት አለመኖር ዘላቂ ሠላም እንዳይኖር ካዳረጉ ምክንያቶች አንዱ ሲሆን አሁን ባለው ፌዴራላዊ ስርዓት ያለው ጥያቄም ትልቅ ያለመግባባት ምንጭ ሆኖ ይታያል። ተመራማሪው እንደሚሉት ለሠላም ግንባታ ጠቃሚ የሆኑ አገር በቀል እሴቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ ሲውሉ አይስተዋልም። በአገሪቷ ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ ሠላምን ስትራቴጂያዊ ጉዳይ አድርጎ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው ለዚህ ደግሞ ጠንካራ ተቋማትን መፍጠር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል። መንግሥት ብቻውን ዘላቂ ሠላም ማረጋገጥ እንደማይችል ጠቁመው ምሁራን፣ ወጣቱንና ኀብረተሰቡን አሳታፊ የሚያደርግ ስርዓት በመዘርጋት በችግሮች ምንጭ ላይ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል። በተለይ የበዳይ ተበዳይ አስተሳሰብ እንዲወገድ በማድረግ የቁርሾና የበቀል አስተሳሰቦች ቦታ እንዳይኖራቸው በመስራት 'ነገን የተሻለ ማድረግ ይጠበቅብናል' ነው ያሉት ዶክተር ግርማ። ዋልታ ረገጥ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸው ልሂቃን በመነጋገርና የሰጥቶ መቀበል መርህን በመከተል ለአገር ሠላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉም ይመክራሉ። የኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ መምህርና የፖለቲካ ምሁር አቶ ግደይ ደገፉ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስርዓት ዴሞክራሲያዊ አለመሆኑ ሠላም እንዳይመጣ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ መሆኑን ያነሳሉ። የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ሠላም ለማምጣት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ። መንግሥትም ቅራኔዎችን የሚፈታበት መንገድ የኃይል ሚዛኑን የጠበቀ ሊሆን እንደሚገባ ነው ምሁሩ ያሳሰቡት። በአገሪቷ ሠላምን በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለመገንባት የአገር ሽማግሌዎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ያሉት ደግሞ የአገር ሽማግሌዎች መድረክ አባል ሼህ ዑመር ዑስማን ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም