1ሺህ 441ኛ የአሹራ በዓል በትግራይ አልነጃሺ መስጊድ ይከበራል

70
መቀሌ (ኢዜአ) ጳጉሜን 2 ቀን 2011---1ሺህ 441ኛ የአሹራ በዓል ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችና ከውጭ የሚመጡ ምዕመናን በተገኙበት ከነገ በስቲያ በትግራይ አልነጃሺ መስጊድ በድምቀት ይከበራል። የአሹራ በዓል በእስልምና ሃይማኖት ወር በገባ በአስረኛ ቀን ጳጉሜን 4 ለፈጣሪያቸው ፀሎት በማድረግ የሚያከብሩት ነው። የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤትና የኢትዮ-ነጃሽ የማልማትና የማስተዋወቅ ፕሮጀክት ትናንት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የአሹራ በዓል በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል። የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሀጂ መሀመድ ካህሳይ እንደገለጹት በወቅቱ የነበሩት ንጉስ አልነጃሽ ከሳዑዲ አገር ተባረው የመጡ ስደተኞችን በመቀበልና የፖለቲካ ጥገኝነት በመስጠት በሰላም እንዲኖሩ አድርገዋል። “ንጉሱ ስደተኞቹ ሃይማኖታቸውን በሰላም እንዲያስፋፉ ከመፍቀዳቸው በተጨማሪ ከሌላ እምነት ተከታዮች በአካባቢው በሰላም፣ በፍቅር፣ በመቻቻልና በእኩልነት እንዲኖሩ በማድረጋቸው ስፍራው በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል” ብለዋል። በመሆኑም በእምነቱ ተከታዮች በየዓመቱ ወር በገባ በአስረኛው ቀን ጳጉሜን 4 ላይ የአሹራ በዓል እንደሚከበር ተናግረዋል። በዓሉ ከአገር ውስጥና ከውጭ የሚመጡ የእምነቱ ተከታዮች አልነጃሽ መስጊድ ተሰባስበው ለፈጣሪያቸው ፀሎት በማድረስ የሚያከብሩት መሆኑንም ሀጂ መሀመድ ተናግረዋል። የኢትዮ ነጃሽ የማልማትና ማስተዋወቅ ፕሮጀክት ሊቀመንበር መምህር ያሲን ራጆ በበኩላቸው በበዓሉ የሚሳተፉ የሀገር ውስጥና የውጭ እንግዶች ከአልነጃሽ በተጨማሪ በክልል የሚገኙ የቱሪዝም መስቦችና የልማት ስራዎችን እንዲጎበኙ ቅድመ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ተናግረዋል። በበዓሉ ላይ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም