በወላይታ ሶዶ ከተማ 35 ኩንታል አደንዛዥ ዕጽ ሲያዘዋውሩ የነበሩ ግለሰቦች ተያዙ

56
ሶዶ እና ድሬዳዋ (ኢዜአ) ጳጉሜን 1 / 2011 በወላይታ ሶዶ ከተማ 35 ኩንታል ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ ዕጽ ሲያዘዋውሩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች ተያዙ። በድሬዳዋ አስተዳደርም ከ146 ኪሎ ግራም በላይ ካነቢስ አደንዛዥ እጽ እንዲቃጠል ተደርጓል። በወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ ምክትል ኢንስፔክተር ህያውሁን ሞጋ እንዳሉት 35 ኩንታል ካናቢሱ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ባለፈው ነሀሴ 25 ቀን 2011ዓ.ም ነው። ዕጹን የሰሌዳ ቁጥሩ 3-03866 አ.አ በሆነ ኤፍ.ኤስ.አር አይሱዙ ተሽከርካሪ ሲያዘዋውሩ የነበሩት አሽከርካሪና ረዳቱ ከነ መኪናው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክተዋል፡፡ ምክትል ኢንስፔክተር ህያውሁን እንዳሉት ካናቢሱን ከኦሮሚያ ክልል ሻሸማኔ ከተማ በማምጣት እስከ አርባ ምንጭና ሞያሌ ከተማ ድረስ የማድረስ ዕቅድ ነበር። ካናቢሱን በአሳቻ ሰዓት በወላይታ ሶዶ ከተማ ለማስተላለፍ ጥረት ሲደረግ በተለምዶ "ቆንቶ" በተባለ የከተማው አካባቢው ከነተሽከርካሪው በፖሊስ ሊያዝ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ስሚንቶ በመጫን ከስር ዕጹን ጭነው በስውር ለማሳለፍ አቅደው የነበረ ቢሆንም ፖሊሶች ባደረጉት ጠንካራ ፍተሻ እጹ ሊያዝ መቻሉንም ምክትል ኢንስፔክተር ህያውሁን አስረድተዋል፡፡ በእጹ ዝውውር ከመነሻው እስከ መድረሻው ድረስ እጃቸው ያለባቸውን አካላት ለማጣራት ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች የክስ መዝገብ ተደራጅቶ የውሳኔ ሂደት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተያያዘ ዜና የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን በተለያየ ጊዜ በቁጥጥር ሥር ያዋለውን ከ146 ኪሎ ግራም በላይ ካነቢስ የተባለ አደንዛዥ ዕፅ እንዲወገድ እድርጓል። የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ማኦ ተሾመ እንደተናገሩት፣ ዛሬ ከከተማው ወጣ ባለ ሥፍራ እንዲቃጠል የተደረገው የካናቢስ ዕፅ 146 ነጥብ 53 ኪሎ ግራም የሚመዝን ነው። ዕፁ በተያዘው ዓመት በድሬዳዋ ከተማ በኩል ወደጅቡቲ ለማጓጓዝ ሲሞከር በቁጥጥር ሥር እንደዋለም ኮሚሽነር ማኦ አስታውሰዋል፡፡ በአደገኛ የዕጽ አዘዋዋሪቹ ላይ ተገቢው ቅጣት መወሰኑንም ተናግረዋል፡፡ እንደምክትል ኮሚሽነር ማኦ ገለፃ የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን ሰንሰለት ከምንጩ ለማድረቅና የከተማውን ሰላም በአስተማማኝ መንገድ ለመጠበቅ የተቀናጀ ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ለእዚህም አደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎችንና ተጠቃሚዎችን ከፍትህ አካላት ጋር በማቀናጀት ዕጾቹ ይዘወተሩባቸዋል ተብለው በሚጠረጠሩ አካባቢዎች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም