አልማ 104 የልማት ፕሮጀክቶች በመገንባት 231 ሺህ ሰዎች ተጠቃሚ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
አልማ 104 የልማት ፕሮጀክቶች በመገንባት 231 ሺህ ሰዎች ተጠቃሚ አደረገ
53
ጵጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም የአማራ ልማት ማህበር በደቡብ ጎንደር ዞን 104 ፕሮጀክቶችን በመገንባት 231 ሺህ ሰዎች ተጠቃሚ ማድረጉን በማህበሩ የደሴ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ገለፀ ። በአማራ ልማት ማህበር የደሴ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባዉ ታደሰ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ማህበሩ የሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች በመንግስት ያልተሸፈኑትና በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ የሚስተዋሉትን ክፍተቶች መሙላት በሚያስችል አቅጣጫ ነው ። በዚህም በደቡብ ወሎ ዞን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 104 የጤና፤ የትምህርትና የዉሃ ተቋማትን በማስገንባትና የሥራ እድል ፈጠራና ሌሎች ፕሮጀክቶችን በመተግበር ከ231 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል። ከተተገበሩት ፕሮጀክቶች መካከል ለ28 ትምህርት ቤቶችና ለ15 ጤና ኬላዎች የተደረገው የማስፋፊያ ግንባታና የቁሳቁስ ማሟላት ስራ ያካትታል ። ስድስት የማምረቻና የመሸጫ ሼዶችን በመገንባት ደግሞ ለተጠቃሚዎች አስተላልፏል ። በተጨማሪም ዘጠኝ አምቡላንሶችን ገዝቶ ለወረዳዎች በማስረከብ ወላድ እናቶችን ወደ ተሻለ የህክምና ተቋማት በወቅቱ እንዲደርሱ እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል። የተጠቀሱት የልማት ስራዎቹን ለማከናወንም ከአባላት መዋጮ የተሰበሰበው 54 ሚሊየን ብር ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል ። ማህበሩ በአዲሱ የበጀት ዓመትም 550 ሚሊዮን ብር ከአባላት በመሰብሰብ የህብረተሰቡን የልማት ችግሮች ለመፍታት አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን አቶ አበባው ታደሰ ተናግረዋል ። ባለፈው ዓመት ግንባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ 106 የተለያዩ ፕሮጀክቶችንም ቅድሚያ ሰጥቶ በማጠናቀቅ የህብረተሰቡን ተቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ በመግለጫዉ ተጠቁሟል፡፡