ለነገ የማይተው የቤት ስራ

91
ታዬ ለማ /ኢዜአ/ ጊዮርጊስ፣ኢትዮጵያ ቡና፣ አዋሳ ከነማና ጅማ አባ ጅፋር፤ በዚህ አመት ደግሞ መቀሌ ሰባ አንደርታ ዋንጫ ሲያነሱ በየአመቱ በክልልም ሆነ በአዲስ አበባ በመገኘት በርካታ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን መከታተሉን ይናገራል  ። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እግር ኳስ ደረጃ እየወረደ ቢመጣም  አሁንም  በአገሪቱ እግር ኳስ ፍቅር ተለክፎ እንደቀረ የሚናገረው  በአዲስ አበባ ስታዲዮም አካባቢ ያገኘውት ብርሃኑ አባተ የተባለው የእግር ኳስ ቤተሰብ ነው  ። "ከማንችስተር ከአርሰናል የተሻለ የአገሪቱ  ክለቦች ጨዋታን ለመከታተል ስታዲየም መገኘት  ስደስተኛል" በማለት ለሀገሩ ኳስ  የተለየ ፍቅር እንዳለው የሚናገረው  ብርሀኑ፤ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በእግር  ኳሱ እየታየ ያለው ስርዓት አልበኝነት ያሳስበኛል ይላል። የፖለቲካ፣  የብሄርና የማንነት ጉዳይ ወደ ስፖርቱ እየገባ መምጣቱ  የሚወደው የእግር ኳስ ሜዳ አሰፈሪ እያደረገው እንደመጣ የተናገረው ብርሃኑ፤ በተለይ በ2011ዓ.ም በእግር ኳስ ላይ የተፈጠረው ውዝግብና ሌሎች ጥፋቶች እንዳሳዘኑትና  በቀጣይ የሚወደውን እግር ኳስ ሳይወድ በግድ እንዲሸሽ ሊያደረገው እንደሚችልም  ስጋቱን ያስረዳል። "ሁለት ሺ አስር አንድ በፕሪምየር ሊጉ ደስ የሚል ነገር አላየሁም፤ ውዝግብ ያልተለየው ከመሆኑ ውጭም ኳስ ሳይሆን ፖለቲካው ጉልቶ የወጣበት ነው “ ሲል በምሬት  ይናገራል፡፡ ደጋፊዎች  ከክለባቸው ጋር ከክልል ወደ ክልል  በነጻነት ተንቀሳቅሰው መደገፍ ያልቻሉበት ሁኔታ መፈጠሩ፤ በአዲስ አበባም ቢሆን ጨዋታዎች በስጋት የተከናወኑበትና የተቋረጡበት ዓመት ሲል የአገሪቱ እግር ኳስ አስችጋሪ  ግዜን እዳሳለፈ ትዝብቱን ይጠቅሳል። የብርሃኑን ሃሳብ የሚጋራው የቀድሞ የብሄራዊ ቡድንና የቅዱስ ጊዮርጊስ የአሁኑ የሃዋሳ ክለብ  ታዋቂው ተጫዋች አዳነ ግርማ ደጋፊዎችን ስጋት ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች በፕርሚየር ሊጉ እየተፈጠሩ  እንደሆነ ይናገራል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ከሰላሳ አንድ አመት በኋላ በደቡብ አፍሪካ እንድትገኝ ጉልህ ሚና የተጫወተው  አዳነ፤ ባለፈው ዓመት በእግር ኳስ ጨዋታዎች ከነበረው ችግር አንጻር ከሜዳ ውጭም ሆነ በሜዳ ውስጥ ከፍተኛ አደጋ አለመድረሱ እድለኝነት ነው ይላል። ኢትዮጵያን  በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ወሳኙንና በውድድሩ ብቸኛዋን ጎል ዛምቢያ ላይ በማስቆጠር መላው ኢትዮጵያውያንን ጮቤ ያስረገጠው አዳነ፤  ባጠቃላይ ያለፈው ዓመት ለእግር ኳስ ከባድ ሲል ነው ዓመቱን  ያስታወሰው። "ሁለት ሺ አስር አንድ እግር ኳሱ በከፍተኛ ችግር የወደቀበት፤ አንድ ቡድን ከሜዳው ውጭ መጫወት የከበደበት፤ ማሸነፍና መሸነፍ ከብሄር ጋርና ከማንነት ጋር ተያይዞ የታየበት አስቸጋር አመት"  ሲል ባልተለመደ በአስቻጋሪ ሁኔታ አመቱ ማለፉን ሲናገር  ፡፡ “አንድ ቡድን ሲሸነፍ ብሄሬ  ተሸነፈ እንጂ ክለቤ ተሸነፈ የሚልበት  ሁኔታ አለመታየቱን፤ ክለቦች ከሜዳ ውጭ የሚያደርጉትን ጨዋታ ማሸነፍ ከባድ የሆነባቸው፤  ከሜዳ ውጭ  መሸነፍ አልያም አቻ መውጣትን ብቻ  አማራጭ አድርገው የሚጫወቱበት“ ሲል  አዳነ አብራርቷል። ክለቦች በሜዳቸው መጫወት አቅቶአቸው በሌላ ሜዳ ለመጫወት  መገደዳቸውን ጨዋታው እግር ኳስ መሆኑ ቀርቶ የፖለቲካ  አስተሳሰቦች ስራመዱበት እንደነበር ጠቅሶ ዳኞችም ቢሆኑ ስጋት ውስጥ ወድቀው የዳኙበት አስቸጋሪ  ግዜ ነበር ይላል የቀድሞ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋች ። ባለፈው አመት ወደ ቀድሞ ክለቡ ሀዋሳ ተመልሶ ሲጫወት ያሳለፈው አዳነ፤ የስፖርት  ሰላም፣ ፍቅርና ጤነኛ ማህበረሰብ መገንባት መርህ  እየተተገበረ አለመሆኑ፤ ከዛ ይልቅ ስፖርቱ ከመርህ ውጭ ሰዎች የሚጣሉበትና ልዩነቶች ጎልቶ የሚታይበት እንደበር አስረድቷል ። ፖለቲከኞችም በእግር ኳስ ውስጥ ገብተው ማውራት መጀመራቸውና  እግር ኮሱን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ሊያደርጉት ሲፈልጉ መስተዋሉንም በመጥቀስ ። ባለፈው ዓመት የእግር ኳስ መርህ ባለመጠበቁ የተፈጠለው ችግር በ2012 እንዲፈጠር መፍቀድ እንደማይገባም ነው አዳነ በአጽኖተ የተናገረው። እግር ኳስ  መለያያ ከመሆኑ ይልቅ፤ አንድነት መፍጠሪያና  ትብብርን ማጠናከሪያ መሆኑን የሚያስረዳው እውቁ ተጨዋች  ስፖርቱ ማስታረቅ የሚችል ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን  ያብራራል፡፡ ታዋቂው የእግር ካስ ተጫዋች ድሮግባን በምሳሌነት በመጥቀስም የስፖርትን መልካም አስተዋጽኦ መጠቀም እንደሚገባ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ "ድርግባ በኮትዲቫር አስቸጋሪ የነበረውን የእርስ በእርስ ጦርነት ስፖርቱን ተጠቅሞ አገሪቱን ሰላም አድርጓል፡፡ ኳስ ማለት ይህ ነው፡፡  ይህን የእግር ኳስ ሃይል እኛም ለፍቅርና  ለሰላም ልንጠቀምበት ይገባል" “ ብሏል፡፡ እኛም እግር  ኳስ አንድነታችንና ህብረታችንን ማጠናከር የሚችል መሆኑን ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካ ዋንጫ ያለፈችበት ወቅት በተጨባጭ መታየቱን የሚያስታውሰው አዳነ  በወቅቱ የነበረውን የአብሮነትና የአንድነት ስሜት ልዩ እንደነበረ  ትዝታውን ይገልጻል ። "ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ ስታልፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ብቻ ሳይሆን በመላው አለም የነበሩት ኢትዮጵያውን ለአገራቸው የነበራቸው ስሜትና አንድነት በጣም የሚገርም ነበር"  ይላል የወቅቱ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ቡድን አባል የነበረው አዳነ። ታዲያ ስፖርቱ ይህን ያህል አቅም ካለው ለምን የመለያያ፣ የጠብ ሜዳ እናደርገዋለን? ሲል የሚጠይቀው ተጨዋቹ ሁሉም ከ2011 መማር አለበት፤ በቀጣይ አመትም ለተሻለ ስፖርት መረባረብ አለብን በማለት ስላለፈው ዓመት በቁጭት ይናገራል። ስፖርቱን ለማዳን  የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎን የሚፈልግ መሆኑን የተናገረው አዳነ፤ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኙች፣ ክለቦችና ዳጋፊዎች መወያየት እንደሚገባቸው፣ ፌድሬሽኑም ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት ማስተማር  እንደሚገባውና  ልክ እንደ ውጪው ዓለም አሰራሮችን በመዘርጋት ለሚፈጠሩ ችግሮች ሃላፊነት የሚወስድ አካል ሊኖር ይገባል ሲልም የምክሩን አሳብ ያካፍላል። “የኢትዮጵያ እግር ኳስ በከፍተኛ ሁኔታ ታሟል፤ ህክምና ያስፈልገዋል”  የሚሉት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ልምድ ያላቸው፤ ብሄራዊ ቡድኑን በአሰልጣኝነት የመሩና  በርካታ ክለቦችን ያሰለጠኑት የአሁኑ የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ  ስዩም ከበደ ናቸው። በየአመቱ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር እየተባባሰ መምጣቱን  በተለይ የስፖርት ማህበረሰቡ መነጋገር ይገባዋል ያሉት አሰልጣኙ ፤ ከቅርብ ግዜ ወዲህ እግር ኳሱ ላይ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር እየታየ፤ ፖለቲካ የሚሸቱ ነገሮች በመከሰታቸው በርካታ ጨዋታዎች በውዝግብ ማለፋቸውን ያስታውሳሉ፡፡ እንደ አዳነ፤ ስዩምና  ብርሀኑ ሁሉ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ የአገራችን እግር ኳስ ውጤት አልባ መሆኑ ሳያንሰን ሌላ ስጋት እየፈጠረ እንደሚገኝ የብዙዎች ትዝብት ነው፡፡ ይህ ውድድር መንግስት ከፍተኛ በጀት መድቦለት ውጤት አልባ መሆኑ ሳያንስ ሰዎች ህይወታቸውን የሚያጡበትና  ፖለቲካ ማራመጃ መሆን እያሳሰባቸው ኳሱ ነገስ እንዴት ይቀጥል ይሆን? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ "እግር ኳሳችን እንደ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ወይም ላሊጋ ይሁን አላልንም፤ ግን ሰላማዊ መድረክ እንዲሆን እንፈልጋለን፤ ተፈንክተን ወይም አደጋ ደርሶብን መውጣት አንፈልግም“ ያለው ብርሀኑ፤  በቀጣይ ዓመት ጨዋታ ከስጋት የነጻ የሆነ ውድድር እንደሚፈልግ ይናገራል። እግር ኳስን ብቻ ለማየት የመጣ ሰው በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት እንዳለበትና ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው ደጋፊ ክብሩና  ሰላሙ ሊጠበቅ ይገባል  ያለው ተዋቂው ተጫዋች አዳነ፤ተጫዋቾችም በሰው ሜዳ ተሳቀውና በፍራቻ ተሸብበው ለመሸነፍ መጫወት እንደሌለባቸውና ያለጭንቀት ከሜዳቸው ውጭ በሰው ሜዳ ላይ ለማሸነፍ መጫወት የሚችሉበት ሁኔታዎች ሊፈጠር እንደሚገባም ይናገራል። ባለፈው አመት በእግር ኳስ ሜዳ የታዩ የተለያዩ ውዝግቦችና ስርዓት አልበኝነት ስፖርቱን ከማቀቀጨጭ በስተቀር ለማንም እንደማይጠቅም የተናገሩት  አሰልጣኝ  ስዩም በ2012 ችግሩ መቀረፍ አለበት ይላሉ። አዳነ እንደሚለው ችግሩን መቅረፍ ፍላጎት ብቻ እንዳይሆን ለተግባራዊነቱ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል። አሰልጣኝ ስዩም ደግሞ ሰላምና ስፖርታዊ ጨዋነት ለድርድር የሚቀርብ ባለመሆኑ ለስፖርቱ ሰላማዊነት ሁሉም ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት ። ይህ ለነገ የማይባለውን የቤት ስራ  መፍቴህ እንዲያገኝ ፌድሬሽን እግር ኳስ ተጨዋቾች አሰልጣኞች ደጋፊዎች እንዲሁም  የፖለቲካ አመራሮችም ከመቼውም ግዜ በላይ ለስፖርቱ ሰላማዊነት የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል። በ2012 ዓ.ም በሀገሪቱ ሰላማዊ የእግር ኳስ ጨዋታ እንዲኖር ለማድረግ ሁሉም ዜጋ ሃላፊነቱን መወጣት ሲችል ነውና ሁላችንም ለውጤታማነቱ ሊንረባረብ ይገባል። ሰላም!  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም