ዻጉሜን እና የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር

737
በቁምልኝ አያሌው (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የምትገኝ የአኩሪ ታሪክ ህብረ ብሄራዊ ማንነት ባለቤት የሆነች ሃገር ናት፡፡ በአህጉራችን አፍሪካም ነፃነታቸውንጠብቀውለመኖርበርካታ ተጋድሎና መስዋትነት ከከፈሉ ሃገራት መካከልም በግንምባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡ በበርሊን ጉባኤ  በኩል የአውሮፓ ሃያላን ሃገራት አፍሪካን እንደስጋ ቅርጫ ሲቀራመቷትና ሲከፋፍሏት ኢትዮጵያ በታላቅ ተጋድሎና ወኔ ነፃነቷን ጠብቃለች። በዚህም ላይቤሪያን በማስከተል ለፀረ-ቅኝ አገዛዝ ወረራ እጄን አልሰጥም ብላ በታሪክ ሰሪ ልጆቿ ተከብራና ነፃነቷን አስጠብቃ የኖረች ድንቅ ምድርም ናት ኢትዮጵያ፡፡ በህዝቦቿ ብዛትም ቢሆን ከናይጀሪያ በመቀጠል ከመላው የአፍሪካ ሃገራት በሁለተኛ ደረጃነት ተቀምጣለች፤ ባላት የቆዳ ስፋት ደግሞ አስረኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ዕድሜያቸው ከአንድ ምዕተ-ዓመት የሚያንስ ሲሆን ኢትዮጵያ ግን ባሳለፈችው ዕድሜና በመንግስታዊ አስተዳደርም ቢሆን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በንጉሠ-ነገሥታት እና ንግሥተ-ነግሥታት ስትመራ የኖረች የሺ ዓመታት ታሪክ ባለቤት ስለ መሆኗም ጭምር መዛግብት ያስረዳሉ። ኢትዮጵያ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጅ የሚኖርባት ምድር ስለመሆኗም ጭምር በርከት ያሉ በሳይንሳዊ ማስረጃነት የተሰነዱ ማረጋገጫዎች ስለመኖራቸውም ነጋሪ አያሻንም። ይህንንም የሰውልጅ ፍልሰት ጥናቶች፣ የቅሪተ-አካል ጥናቶችና ሌሎች የሳይንሳዊ ዘዴ ማስረጃዎች ካረጋገጡልንም ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከ80 በላይ ብሄር ብሄረሰብ ያሏት ሀገራችን ኢትዮጵያበአሁኑ ሰዓት ፌደራላዊ የመንግስት አስተዳደር ስርዓት በመከተል ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥራለች፡፡ኢትዮጵያ ባሏት ህብረ-ብሄራዊ ማንነት የብሄረሰቦች ሙዚየም የምትሰኝ ሲሆን አማራው፣ ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ ሶማሌው፣ ወላይታው፣ ሲዳማው፣ ዶርዜው፣ ...እና ሌሎች ያልተጠቀሱየማህበረሰብ ክፍሎችም ጭምር በአብሮነት፣ በአንድነትና በመቻቻል የሚኖሩባትአኩሪና የበረከት ምድር ነች፡፡ በአምልኮተ-ሃይማኖትም ቢሆን ክርስትና እና እስልምና ሃይማኖቶች ለዘመናት አብረው መኖራቸውን ዞረን ስናይ እጅግ ልዩ ኩራት እንዲሰማን ያደርጋል፡፡ኢትዮጵያ ከሌላ ዓለማት በተለየ መልኩ የአስራ ሶስት ወር ፀጋ ባለቤት መሆኗን ስናይ ደግሞሚስጠራዊነቷን ከቶ ለመመስከር የሚቸገር ያለ አይመስለንም፡፡ኢትዮጵያ ልክ እንደሌሎች ዓለማት የጊዜ አቆጣጠር ቀመሯበቀን፣ በሳምንት፣ በወር እና በዓመት የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌበኢትዮጵያአቆጣጠር 2012 ዓመተምኅረት ቢሆን እንደአውሮፓውያንየዘመንአቆጣጠር ደግሞበከፊል 2019 እ.ኤ.አ. እና2020 እ.ኤ.አ. ይሆናል። በዓለም ላይ እስካሁን ድረስ በርካታ የዘመን አቆጣጠር አለ፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር፣ ጎሪጎሪያን ካሌንደር፣ የቻይና ዓመት አቆጣጠርና ሌሎችም እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የሃገራችን ኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከሌሎች ዓለማት ለምን ተለየ? ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ባሕረ ሐሳብ በሚል መጽሐፋቸው ላይ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከምዕራባውያን የተለየበትን ምክንያት ሲገልጹ “ሮማውያን የሮም ከተማ የተቆረቆረችበትን ዘመን መነሻ አድርገው ይጠቀማሉ፤ ታላቁ እስክንድርም የገነነበት ዘመን መቁጠሪያቸው ሆኖ ነበር” የእኛ ካህናትም ዘመነ እስክንድር በሚል ይጠቀሙበት እንደነበር መፃህፍትይመሰክራሉ፡፡ሶርያውያን የዘመን አቆጣጠራቸውን የሚለኩት በፀሐይ ቆጥረው ለዓመቱ 365 ቀን ከ6 አካፍለ ው ዕለትን በመስጠት ከሮማውያን በተዋሱት ጊዜ የዓመቱን መጀመሪያ አዲስ ዓመት ይሉታል፡፡ በኋላ የሰማዕታት መታሰቢያ እንዲሆን በ460 ዓመተ እግዚእ የተባለውን የዘመን መለወጫ ወደ መስከረም 1 ቀን ለወጡት ይባላል፡፡ የሀገራችን ሊህቃንም አዲስ ዓመታችን መስከረም አንድ ቀን እንዲሆን የወሰኑት ይኸንን በመከተል እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ የዓመቱን መጀመሪያ መስከረም ማድረግን ከሶርያውያንም ሆነ ከግብጾች ብናገኘውም ጀማሪው በ46 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ይገዛ የነበረው ዩልዮስ ቄሣር ስለነበር በዩልዮስ ባሕረ ሐሳብ ተብሎ ይጠራል፡፡ ዩልዮስ ቄሣር በ46 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ባወጣው የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት መሠረት ዓመቱን 365 ዕለት ከ6 ሰዓት አድርጎ ለአራት ወራት 30 ቀናት መድቦ ለአንዱ 28 ቀን በ4 ዓመት አንዴ ደግሞ 29 ቀናት በመስጠት ለቀሩት ሰባት ወራት 31 ቀናት መድቦላቸው በ12 ቦታ ከፋፍሏቸዋል፡፡ አውሮፓውያኑ የሚጠቀሙበትም ይህን አቆጣጠር መነሻ አድርገው ነው፡፡ የእኛ ዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያን እንዴት እንደተለየ አሥራት ገብረማርያም የዘመን አቆጣጠር በሚለው መጽሐፋቸው ሲገልጹ “ዲዮናስዮስ የተባለው የሮም መነኩሴ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተወለደበት ዘመን በስሌት ለመድረስ የተከተለው መንገድ እንደነበር ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት ዘመን ለመወሰን የታሪክ ክስተትን አልተከተለችም፡፡ ቤተክርስቲያኗ የተከተለችው ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን 5500 ዘመንን ነው” በማለት የልዩነቱን ምክንያት አስረድተዋል፡፡ የዘመን አቆጣጠር ልዩነት መነሻው የዚህ ክስተት መሆኑን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲያረጋግጡ “ኢትዮጵያ ዘመነ ብሉይን እንዲህ አስከትላ 5500 ብላ ስትቆጥር ዘመነ ሐዲስ ልዩ ሆኖ ከማንም ቁጥር አይገጥምም፡፡ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ከምስራቆቹም ከምዕራቦቹም ሁልጊዜ በሰባት ዓመትታ ጎድላለች፡፡ ምክንያቱም ባለ ታሪኮችን ትታ ወንጌል ተርጓሚዎችን መነሻዋ ስላደረገች ነው” ይላሉ፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያና የአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ልዩነት ሊኖረው እንደቻለ ለማወቅ ይቻላል። ወደ ሃገራችን የዘመንና ወራት አቆጣጠር ስንመለስኢትዮጵያ የአስራ ሶስት ወር ፀጋና ባለቤት መሆኗ ከሌሎች ልዩ ያደርጋታል፡፡ ወራቶቹም ከጳጉሜ በስተቀር የራሳቸውን ኢትዮጵያዊ ስምና ስያሜ በመያዝ መስከረም፣ ጥቅምት፣ ህዳር፣ ታህሳስ፣ ጥር፣ የካቲት፣ መጋቢት፣ ሚያዚያ፣ ግንቦት፣ ሰኔ፣ ሃምሌ፣ ነሃሴና ጳጉሜ በመባል ይጠራሉ፡፡ ኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርጓትን የዘመን አቆጣጠር ስንመለከትከመስከረም እስከ ነሃሴ ያሉ ወራቶች በ30 ቀናት የተከፈሉና ኢትዮጵያዊ ስምና ስያሜ አሏቸው፤ ጳጉሜ ወር ግንበየዓመቱ 5 ቀናትን ስትይዝ በየአራት ዓመት አንዴ 6 ቀንና በየስድስት መቶ ዓመት አንዴ ደግሞ ሰባት እንደምትሆን የዘመን አቆጣጠርሂደታችን ያሳያል፡፡ በሃገራችን የወራት አቆጣጠር ከነሃሴ በመቀጠል ሲያሻት በአራት ዓመት አንዴ ስድስት በየአመቱ አምስትና ስትፈልግ ደግሞ በየስድስት መቶ ዓመት አንዴ ሰባት የምትሆን ሚስጥራዊና ተቀያያሪ ጠባይ ያላት ወር አለች፤ ያችም ጳጉሜ ትባላለች፡፡ጳጉሜ ተብላ የምትጠራው ወር ስያሜዋን ያገኘችው “ኤፓጉሜኔ” ከሚል የግሪክ ቃል መሆኑን ይነገራል፡፡ይህ መሆኑ ደግሞ በስምና ስያሜ ረገድ ከሌሎች የኢትጵያ ወራቶች ልዩ ያደርጋታል፡፡“ኤፓጉሜኔ” የሚለው የግሪክ ቃል ትርጓሜ ደግሞ ጭማሪ ማለትእንደሆነ ይታመናል፡፡ በአራት ዓመት አንዴ ማለትም በዘመነ ዮሐንስ ጳጉሜ ስድስት ቀን ትሆናለች፡፡ አውሮፓዊያን ጳጉሜን በየወሩ ሠላሳ አንድ ቀን በማድረግ ተጨማሪ ሲያደርጓት ኢትዮጵያ ደግሞ በየዓመቱ ተጨማሪ ወር አድርጋ ሰይማታለች፡፡ይህም ጳጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማውን የክረምት ወቅት የምናልፍባት ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ ድልድይም ነች ፡፡ በዚህም ሃገራችን ኢትዮጵያ የአስራ ሦስት ወራት ፀጋ ወይም Thirty months of sunshine እንድትባል አስችሏታል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጰያን የዘመን አቆጣጠር ለየት ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ ጳጉሜ የምትባል ወር ስላለች መሆኑን ልብ ይሏል። ስለ ጳጉሜ አጠቃላይ ሁኔታ ስንመለከት ጳጉሜ የወር ስም ሆና በነሃሴና በመስከረም ወራት መካከል የምትገኝና በኢትዮጵያ የወራት አቆጣጠር የመጨረሻና አስራ ሶስተኛ የወር ስም ሆና ተሰይማለች፡፡ ኢትዮጵዊያን ይህችን ጳጉሜ ወር የምህረትና ወደ አዲስ አመት መሸጋገሪያና መግቢያ የተስፋ ወር ነች በማለት ይጠሯታል፡፡ እንዲያውም ጳጉሜ ከሌሎች ወራቶችም ቢሆን ለየት የሚያደርጋት ትንሽ ቀናቶች ያሏትና ወርሃዊና ሃይማኖታዊ በዓላት የሌላት ብቸኛ ኢትጵያዊ ወርም ጭምር ናት፡፡ ስያሜዋንም ስንመለከት ከሌሎች የኢትያጵያ ወራቶች በተለየ መልኩ ኢትዮጵያዊ ስያሜ አይደለም፡፡ በዚህ ሂደትም በሁለት ዘመናት መካከል የምትገኝ እንደመሸጋገሪያ ድልድይ የምታገለግል ወር ናት ጳጉሜ፡፡ይህች ወር ዓዲስ ዓመትን ለመቀበል በኢትዮጰያዊያን ዘንድ ሽርጉዱ የሚበዛባት ገበያው የሚደራባት ወር በመሆኗም ልዩ ያደርጋታል፡፡ያው አዲስ ዓመት ሲመጣ ደግሞ በርካታ ሁነቶችም ይስተናገዳሉ፡፡ የዻጉሜን ወር ኢትዮዽያዊ ወር ናት የተባለበት ምክንያትም ሃገራችንን ከሌሎች በዘመን አቆጣጠር ለየት ብላ እንድትታይ ያደረገች በመሆኗ ነው። በሌላም በኩል በእኛ የዘመን አቆጣጠር የወር ደሞዝ የሚቀበሉ ሰዎች ዻጉሜን አምስት ስትሆን አምስቱን ቀናት እንዲሁ እንደ ዘንድሮ ስድስት ስትሆን ደግሞ የተጠቀሱትን ቀናት ያለ ደሞዝ አገልግሎታቸውን ያበረክታሉ። በዚህም ሳቢያ የዻጉሜን ወር መስሪያ ቤቶቻቸውን በበጎ ፈቃድ ለማገልገል ዕድሉን እንዳመቻቸች እንታዘባለን። ከዚህም ከፍ ባለ ወሯ ወደ አዲስ አመት መሸጋገሪያ እንደመሆኗ መጪው አመት የሰላም፣ የበረከት፣ የብልፅግና ይሆን ዘንድ ምዕመናን በፀሎት የሚተጉባት ጭምር ናት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመንግስት ደረጃ ዻጉሜን እና ቀናቶቿ የተለያዩ ስያሜዎችን በመያዝ እየተከበሩ ይገኛሉ። ዘንድሮም የመጀመሪያዋ የዻጉሜን ቀን ‘የብልፅግና ቀን’ በመባል ስትሰየም፣ ሁለተኛዋ ቀን ደግሞ ‘የሰላም ቀን’ ስያሜን እንድትይዝ ተደርጓል። የዚህች አጭር ወር ሶስተኛ ቀን ‘የሃገራዊ ኩራት ቀን’ ተብሎ የተጠራ ሲሆን አራተኛዋ ቀንም እንዲሁ ስያሜዋ ‘የዲሞክራሲ ቀን’ ተብላለች። ‘የፍትህ ቀን’የሚል ስያሜን ያገኘችው ደግሞ የወሯ አምስተኛ ቀን ናት። ከሁሉ ከሁሉ ስድስተኛዋ ቀን አሁን እጅግ የሚያስፈልገን ስያሜን ይዛለች ‘የአንድነት ቀን’ በመባል ማለት ነው። መጪው አዲስ አመት ፍትህ ዲሞክራሲና ሰላሟን ያሰፈነች እንዲሁም በብልጽግና ጎዳና በኩራት የምትራመድ ሃገርን በተጠናከረ አንድነት ላይ የተመሰረተች ሃገር እንድትኖረን እርስ በርሳችን ተከባብረን በፍቅር እንድንኖር ፈጣሪ ይርዳን። መልካም አዲስ አመት!!!!!        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም