ለአሜሪካ ታላላቅ ኩባንያዎች ስለ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እድሎች ማብራሪያ ተሰጠ

75
አሜሪካ ሰኔ 7/10/2010 በአሜሪካ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ከበርካታ ታዋቂ የአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር በቺካጎ ውይይት አድርገዋል፡፡ አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ስላሉት የኢንቨስትመንት እድሎች ለኩባንያዎቹ ማብራሪያ መስጠታቸውን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የላከው መረጃ የሚገልጸው። ስብሰባውን ያዘጋጀው የቺካጎ ዓለም ዓቀፍ ጉዳዮች ምክር ቤት ሲሆን ከምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ኢቮ ዳልደር ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ ምክር ቤቱ በሚቀጥለው የበጀት ዓመት አንድ የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ማቀዱም ተጠቅሷል። በቺካጎ ከሚገኝ አንድ የጸሃይ ሃይል ኩባንያ ስራ አስፈጻሚ ጋርም ውይይት ተደርጓል፡፡ ኩባንያው በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች ለመስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ጥናት በማካሄድ ላይ መሆኑ ነው የተገለጸው። አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን በኢሊኖስ ቴክኖሎጂ ተቋም ያለውን የጸሃይ ኃይል ቴክኖሎጂን ጎብኝተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በቱርክ የኢፌዲሪ አምባሳደር አያሌው ጎበዜ ሳንኮን ከተሰኘ በቱርክ የሚገኝ ኩባንያ ፕሬዝዳንት ናዛኬት ኤሚን ጋር ተወያይተዋል። ፕሬዝዳንቷ በአገራችን ስላሉ የቢዝነስ እድሎችና አማራጮች ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን፤ በአገራችን እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አድንቀው ለተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶች የሚውል ብድር እና ፋይናንስ ለማቅረብ ያላቸውን ፍላጎት ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም